ዜናፖለቲካ

ዜና: አቶ ጌታቸው ረዳ የክልሉን የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊን ማሰናበታቸውን አስታወቁ፣ ቢሮው የጊዜያዊ አስተዳደሩን መዋቅር በማፍረስ ተጠምዷል ሲሉ ተችተዋል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3/2017 ዓ.ም፡- የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የክልሉን የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ የሆኑትን ሌተናል ጀነራል ፍስሃ ኪዳኑን ከሃላፊነት ማንሳታቸውን ትላንት መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም በጻፉት ደብዳቤ አስታወቁ፤ “የቢሮው ሃላፊ ወገንተኝነታቸው የማን እንደሆነ በግልጽ አሳይተዋል” ሲል ተችተዋል።

የጸጥታ ቢሮው “የመንግስትን ትዕዛዝ ከማክበር ይልቅ የመንግስትን መዋቅር ማፍረስ ላይ ተጠምዷል፣ ይህንንም የህግ ማስከበር ስራ አስመስሎ እያቀረበ ይገኛል” ሲሉ ኮንነዋል፤ “የቢሮው ሃላፊ ወገንተኝነታቸው የማን እንደሆነ በግልጽ ያሳያል” ሲሉ ባወጡት መግለጫ ተችተዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ በክልሉ በተለያዩ ግንባሮች አዛዦች መሆናቸው የተገለጸ ሶስት ጄነራሎችን ሜጀር ጀነራል ዮሃንስ ወ/ጊዮርጊሰ፣ ሜጀር ጀነራል ማሾ በየነ እና ብርጋዴር ጀነራል ምግበይ ሀይለ በግዜያዊነት ማገዳቸውን ማስታወቃቸውን የተመለከተ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ባወጣው መግለጫ እግዱ ተቋማዊ አሰራርን እና ህግን ያልተከተለ ነው ሲል እንደማይቀበለው ማስታወቁን በዘገባችን ተካቷል።

የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ “የወንጀለኞች ጠበቃ መሆን ይብቃ” በሚል ርዕስ መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ውሳኔውን እንደማይቀበለው በመግለጽ “የእግድ እርምጃ የተላለፈው በወንጀለኞች ላይ የተግባር እርምጃ መውሰድ ስለተጀመረ ነው” ማለቱ ይታወቃል።

የሰላም እና ጸጥታ ቢሮውን መግለጫ ተከትሎ ግዜያዊ አስተዳደሩ ትላንት መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ቢሮውን ተችቷል፤ ቢሮው “የጊዜያዊ አስተዳደሩ አካል ሳይሆን የአንድ ቡድን የወታደራዊ ክንፍ መሆኑን በግልጽ ያሳየ ነው” ሲል ኮንኗል።

የቢሮው ሃላፊ ግልጽ መረጃ የተገኘባቸው በመሬት ወረራ፣ በብረታ ብረት ስርቆት፣ በእርዳታ እህል  ስርቆት፣ በማዕድን ስርቆት፣ በተፈጥሮ ሃብት ማውደም፣ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲሁም በህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የተሳተፉ እና በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በመንግስት የተሰጣቸውን ትዕዛዝ አልተገበሩም ሲል ተችቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“የመንግስትን ትዕዛዝ ከማክበር ይልቅ የመንግስትን መዋቅር ማፍረስ ላይ ተጠምዷል፣ ይህንንም የህግ ማስከበር ስራ አስመስሎ እያቀረበ ይገኛል” ሲል ኮንኗል፤ “የቢሮው ሃላፊ ወገንተኝነታቸው የማን እንደሆነ በግልጽ ያሳያል” ሲል አስታውቋል።

የሰላም እና ጸጥታ ቢሮው መግለጫ በህግም፣ በሞራልም ይሁን ፖለቲካዊ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ በፍጥነት ሊታረም ይገባዋል ሲል አሳስቧል።

በሌላ ዜና በትግራይ ክልል በአንዳንድ ከተሞች ትላንት ግጭቶች መከሰታቸው የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ባቀረቡት ዘገባ አስታውቀዋል።

በክልሉ ደቡብ ምስራቅ ዞን በምትገኘው አዲጉዶም ከተማ በጸጥታ ሀይሎች እና በከተማዋ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ተሿሚዎች በሚደግፉ ነዋሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት አምስት ሰዎች በጥይት ተመትተው መቁሰላቸውን መቀለ ኤፍኤም 104 ሬድዮ በዘገባው አስታውቋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፀጋይ ገ/ተኽለ ነግረውኛል ብሎ ሬድዮ ጣቢያው ባስደመጠው ዘገባው ከቆሰሉት መካከል ሁለቱ ወደ መቀለ አይደር ሪፈራል ሆስፒታል መላካቸውን አስታውቋል።

አስተዳዳሪው ስለሁኔታው ሲያስረዱ “የአዲግዶም ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በስብሰባ ላይ እያለ የትግራይ ሰራዊት ታጣቂዎች መጥተው የቢሮ ቁልፍ እና ማህተም እንዲያስረክቡ ማዘዛቸውን እና የካቢኔ አባላቱ ደግሞ አናስረክብም በማለታቸው የቶክስ ሩምታ ተከፍቷል” ብለዋል።

በተኩሱም አምስት ሰዎች ቆስለዋል፣ በርካቶች ደግሞ ተደብድበዋል ሲሉ ገልጸዋል፤ የካቢኔ አባላቱን በፓትሮል መኪና ጭነው ወስደዋቸዋል፣ የት እንዳደረሷቸው የሚታወቅ ነገር የለም ሲሉ አስታውቀዋል።   

በተመሳሳይ በአዲግራት ከተማ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሾማቸውን ከንቲባ በማውረድ በነደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የህወሓት ቡድን የተሾሙት አቶ ረዳኢ ገ/እግዚአብሔር ስራ መጀመራቸውን የተመለከተ መረጃ ወይን ጋዜጣ አሰራጭቷል። ከንቲባው መደበኛ ስራቸውን ትላንት መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምረዋል ብሏል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button