ማህበራዊ ጉዳይዜናፖለቲካ

ዜና: የወረባቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፈንታው ከበደን ጨምሮ ሶስት ሰዎች በታጣቂዎች በተፈጸመባቸው ጥቃት ተገደሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3/2017 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የወረባቦ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ፈንታው ከበደን ጨምሮ ሶስት ሰዎች ትናንት መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም በታጣቂዎች በተፈጸመባቸው ጥቃት መገደላቸውን የወረባቦ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ።

የአስተዳደሩ ኮሚኒኬሽን በይፋዊ የፌስቡክ ድረገጹ ላይ ትናንት ማምሻውን ባወጣው የሀዘን መግለጫ እንዳስታወቀው የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ፈንታው ከበደ፣ የወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አድስ ዘመን ፍሰሃ እና ሹፌር አቶ ከበደ እንድሪስ የተገደሉት ለመስክ ስራ በወጡበት ወቅት “የታጠቁ ፅንፈኛ ሃይሎች” ባደረሱባቸው ጥቃት ነው ብሏል።

“ህዝብን ለማገልገል ደፋ ቀና ሲሉ በጉዞ ላይ የነበሩ የወረዳ አመራርና ባለሙያዎችን መንገድ ላይ አድፍጠው ጠብቀው ገድለዋቸዋል” ያለው መግለጫው፤ “ፅንፈኛ ሀይሎች በሀሳብ ትግል ማሽነፍ ያልቻሉትን በጠመንጃ ለማስፈፀም መሪ በሄደበት እየጠበቁ ተደብቀው ጥቃት በማድረስና በመግደል አላማቸውን ለማሳካት እየጣሩ ይገኛል” ሲል አክሏል።

አያይዞም “ለህዝቡ ልማት፣ ሠላምና አንድነት የሚተጉ፣ ህዝቡ ተስፋ የሚጥልባቸውን መሪዎችን በመግደል ትግሉን ማስቆም አይቻልም” ብሏል።

በአማራ ክልል በመንግሥት የጸጥታ አካላት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለውን ግጭት ተከትሎ በክልሉ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች ላይ እየተፈጸሙ የሚገኙት ጥቃቶች ተባብሰው ቀጥለዋል።

ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የቆቦ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ደርቤ በለጠ ህዳር 1 ቀን 2017 ዓ.ም በታጣቂዎች በተተኮሰባቸው ጥይት መገደላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በወቅቱ የቆቦ ከተማ የብልጽግና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ ደርቤ በለጠ ከጠዋቱ 4 ሰዓት አከባቢ ቆቦ ከተማ በሚገኘው ሚኪኤሌ ሰለሞን ሆቴል ቁርስ እየተመገቡ ባለበት ወቅት በተተኮሰባቸው ጥይት መገደላቸውን ዘገባው አመልክቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

እንዲሁም በክልሉ የሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ አስተዳደር ፅህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት ወ/ሮ ሚሊሹ በቀለ ግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም በታጠቁ ሰዎች መገደላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በተመሳሳይ መልኩ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በዞኑ የሚገኘው ኤፍራታ ግድም ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ አልብስ አደፍራሽ በአከባቢው በሚንቀሳቀሱ ሀይሎች  መገደላቸው ይታወሳል።

በተጨማሪም በሰኔ ወር 2015 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ዞን የሸዋሮቢት ከተማ ሁለት የተለያዩ የመንግስት የፀጥታ ዘርፍ የስራ ሃላፊዎች መገደላቸው አይዘነጋም፡፡

በተመሳሳይ ምክትል ሳጅን ያለለት ደጉ ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም በሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ባልታወቁ ግለሰቦች በጥይት ተደግለዋል፡፡

እንዲሁም የሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት የስራ ባልደረባ የሆነችው ወ/ሪት ጽዮን ተገኝ እና የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ውብሸት አያሌው በተለያያ ጊዜ ማንነታቸው ባልታወቀ ግለሰቦች በተተኮሰባቸው ጥይት መገደላቸው ይታወሳል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button