ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: ጊዜያዊ አስተዳደሩ “በክልሉ የሚገኙ ሁለት ግንባር አዛዦች” እንቅስቃሴ ወደ ከፋ ሁኔታ እየተሸጋገረ ነው፣ የፌደራል መንግስት እገዛ ሊያደርግልኝ ይገባል ሲል ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3/2017 ዓ.ም፡- የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ “ሰሜን ምስራቅ እና ደቡብ ግንባር አዛዦች እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ በከፋ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል” ሲል ዛሬ መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

“ሁኔታውን ለመከላከል በተለይም ደግሞ የክልሉ ወጣቶች እና የሰራዊቱ አባላት ተደራጅተው አከባቢያቸውን እንዲጠብቁ” ሲል አሳስቧል፤ “የሁለቱን ግንባር አዛዦች ለመታገል እንዲሰለፍ” ሲል ጥሪ አቅርቧል።

“በውስጥ እና በውጭ ያላችሁ የክልሉ ተወላጅ በጠቅላላ፤ የክልሉ ወጣቶች እና የሰራዊቱ አባለት ደግሞ በተለይ ሁኔታውን በደንብ ተገንዝባችሁ አከባቢያችሁን እራሳቸሁ ጠብቁ” ሲል አሳስቧል።

“የሁለቱ ግንባር አዛዦችን ለመዋጋት እንድትሰለፉ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጥሪ ያቀርባል” ብሏል።

“የፌደራል መንግስቱም በጸጥታ ሀይሉ ስም እይተንቀሳቀሱ ያሉት አካላት የአንድ ኋላቀር እና ወንጀለኛ ቡድን ተላላኪዎች እንጂ የጊዜያዊ አስተዳደሩንም ሆነ የትግራይ ህዝብን የማይወክሉ መሆናቸውን ተረድቶ አስፈላጊውን እገዛ ሊያደርግ ይገባዋል” ሲል አሳስቧል።

“የፕሪቶርያው ስምምነት ሲጣስ እና የትግራይ ህዝብ ለተጨማሪ ጥፋት ሲዳረግ እያየ ዝም ሊል አይገባም” ብሏል።

አለምአቀፉ ማህበረሰብም በተመሳሳይ ቡድኑ የፕሪቶርያውን ስምምነት እያፈረሰው ስለሆነ አስፈላጊውነ ጫና ሊያሳርፍባቸው የገባል ሲል አስታውቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“ከጥር 15 ቀን 2017 ጀምሮ አንዳንድ የትግራይ ሰራዊት ከፍተኛ አዛዦች የጥቂቶችን  የስልጣን ጥማት ለማርካት ግልጽ የሆነ መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ነበር” ሲል ያወሳው መግለጫው በዚህ ሳምንት ግን “በተለይ የሰሜን ምስራቅ እና ደቡብ ግንባር አዛዦች የሚመሩ ህገወጥ ድርጊቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል” ሲል አስታውቋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህንን አደገኛ ያለውን ድርጊት ለመግታት እና ለማስቆም የካቲት 26 ቀን 2007 ዓ.ም ለትግራይ ጦር ዋና አዛዥ ደብዳቤ መጻፉን አመላክቷል፤ ሁኔታው እልባት ባለማግኘቱ የግንባሩ አዛዦች ላይ እግድ መጣሉን፣ የጸጥታ ቢሮ ኃላፊውንም ከኃላፊነታቸው ማንሳቱን ጠቁሟል።

አሁንም በሰላማዊ የክልሉ ነዋሪ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ቀጥሏል ያለው መግለጫው ከላይ እስከ ታች የጊዜያዊ አስተዳደሩን መዋቅር የማፍረስ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብሏል።

የሰራዊቱ ከፍተኛ አዛዦች የአንድን የስልጣን ጥመኛ ቡድን ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ የጊዜያዊ አስተዳደሩ መዋቅር እንዲፈርስ እና የፕሪቶርያው ስምምነት በግልጽ እንዲጣስ በማድረግ የትግራይን ህዝብ ለዳግም ስቃይ እያስገቡት ይገኛል ብሏል።

ከትላንት መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምረው የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮችን እያደኑ፣ እያፈኑ እና እያሰሩ ይገኛሉ ሲል አስታውቋል፤ ቡድኑ እድል ካገኘ የጊዜያዊ አስተዳደሩን አመራሮች ለሶስተኛ ወገን አሳልፊ ከመስጠት እንደማይመለስ መገንዘብ ያስፈልጋል ብሏል

“በትግራይ ሰራዊት አዛዦች ስም እየተካሄደ ያለው ዘመቻ ሁኔታዎች ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ቁጥጥር ውጭ እንዲወጡ በማድረግ እንደ ህዝብ እርስ በርሳችን እንድንባላ እና እንድንጨራረስ የሚያደርግ ሃላፊነት ተጎደለው፣ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው” ሲል ኮንኗል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የክልሉን የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ የሆኑትን ሌተናል ጀነራል ፍስሃ ኪዳኑን ከሃላፊነት ማንሳታቸውን የተመለከተ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል፤ ፕሬዝዳንቱ “የቢሮው ሃላፊ ወገንተኝነታቸው የማን እንደሆነ በግልጽ አሳይተዋል” ሲል መተቸታቸውንም ዘገባው አካቷል።

በተመሳሳይ አቶ ጌታቸው ረዳ በክልሉ በተለያዩ ግንባሮች አዛዦች መሆናቸው የተገለጸ ሶስት ጄነራሎችን ሜጀር ጀነራል ዮሃንስ ወ/ጊዮርጊሰ፣ ሜጀር ጀነራል ማሾ በየነ እና ብርጋዴር ጀነራል ምግበይ ሀይለ በግዜያዊነት ማገዳቸውን ማስታወቃቸውን የተመለከተ ዘገባ ማቅረባችንም ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ባወጣው መግለጫ እግዱ ተቋማዊ አሰራርን እና ህግን ያልተከተለ ነው ሲል እንደማይቀበለው ማስታወቁን በዘገባችን ተካቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button