
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3/2017 ዓ/ም፦ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፌዴራል መንግስት “አስፈላጊውን ድጋፍ” እንዲያደርግለት መጠየቁን ተከትሎ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) “በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሶስተኛ ወገን ትግራይ ውስጥ እጁን እንዲያስገባ የሚያደርገው ጥሪ በፍፁም ተቀባይነት የለዉም” ሲል ተቃወመ።
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ትናንት 03 መጋቢት 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፤ በጊዜያዊ አስተዳደሩ አራት የሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች መታገዳቸው “ከሃላፊነት ውጪ የተደረገና ተፈፃሚነት የሌለው” ውሳኔ ነው ሲል ገልጿል።
ውሳኔው እጅግ አደገኛ ነው ሲል የገለጸው ህወሓት ክልላዊ፣ አገራዊ እና ቀጣናዊ ሁኔታዎች እጅግ በተወሳሰቡበት በአሁኑ ወቅት “ሃላፊነት በጎደለው መንገድ ሰራዊቱን ያለ አመራር በማስቀረት ህዝባችንን ለከፋ የህልውና አደጋ ለማጋለጥ ያለመ ሆን ተብሎ የተፈፀመ አደገኛ ስራ መሆኑ ህዝቡና ሰራዊቱ ሊገነዘበው ይገባል” ሲልም አሳስቧል፡፡
አክሎም፤ የትግራይ ሕገ-መንግስትን በመጣስ “የተወሰኑ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ኣመራሮች ከተልዕኳቸው ወጥተው የውጪ ሃይሎች መሳሪያ በመሆን የትግራይ ህዝብን ብሄራዊ ጥቅም ኣሰልፈው እየሰጡ ነው” ሲል ከሷል። እንደዚሁም የትግራይ ሕገ-መንግስትን በመጣስ በክልሉ “ማቆሚያ የሌለው ኣደገኛ ሁኔታ እየፈጠሩ ነው” በሰራዊቱና በአመራሩ ላይ ያነጣጠረ “ስም ማጥፋትና ማጥላላት፣ እንደዚሁም ማስፈራራት” በተቀናጀ መንገድ ሲነዛ ቆይቷል ብሏል፡፡
ይህ መግለጫ የተሰጠው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በትግራይ ወታደራዊ ኃይሎች ውስጥ ያሉ አካላት “የፕሪቶሪያ ስምምነትን ለማፍረስ እና ክልሉ እንዳይረጋጋ እየሰሩ” መሆናቸውን መገልጹን ተከትሎ ነው። “ከጥር 15 ቀን 2017 ጀምሮ አንዳንድ የትግራይ ሰራዊት ከፍተኛ አዛዦች የጥቂቶችን የስልጣን ጥማት ለማርካት ግልጽ የሆነ መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ነበር” ሲል ያወሳው መግለጫው በዚህ ሳምንት ግን “በተለይ የሰሜን ምስራቅ እና ደቡብ ግንባር አዛዦች የሚመሩ ህገወጥ ድርጊቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል” ሲል አስታውቋል።
የፌዴራል መንግስት እየተባባሰ የመጣውን ቀውስ “እንዲረዳ” እና ሁኔታው የበለጠ እንዳይባባስ ለመከላከል “አስፈላጊውን ድጋፍ” እንዲያደርግ አሳስቧል። አስተዳደሩ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “አስፈላጊ ጫና እንዲፈጥር” ጥሪ ያቀረበ ሲሆን እርምጃ አለመውሰዱ ለትግራይ ህዝብ “ሌላ ዙር ስቃይ” ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቋል።
ይሁን እንጂ ህወሓት በመግለጫው ትግራይ ውስጥ የተጀመረው ህግና ስርዓት የማስከበር ስራ ግዚያዊ አስተዳደሩና የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የሚያፈርስ ሳይሆን የተጀመረውን የሰላም ስምምነት ትግበራ ይበልጥ የሚያጠናክር፣ የትግራይ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት የሚያስከብር፣ የህግ የበላይነትና ተጠያቂነት የሚያረጋግጥ፣ በትግራይ ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ የሚያሰፍን እና ብሄራዊ ጥቅሞቻችን ለማስጠበቅ የሚያስችል ነው ብሏል፡፡ ፓርቲው አክሎም ግዚያዊ አስተዳደሩ፤ ህወሓትና የትግራይ ሰራዊትን በመወንጀል “ትግራይ ውስጥ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ሁኔታ ሊያጋጥም እንደሚችል” በመግለፅ “እያደናገረ ሶስተኛ ወገን ወደ ትግራይ እንዲገባ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ጥሪ እያደረገ ነው” ሲል ተችቷል፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያ መንግስትና የዓለም ማህበረሰብ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት “በሙሉነትና በፍጥነት በመተግበር ወደ ዘላቂ ሰላምና መልሶ መቋቋም” በሚወስድ መንገድ አወንታዊ ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል። አክሎም መላው ትግራይ ህዝብ “ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ለማስከበር፣ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ፣ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን በሚደረጉ ስራዎች እንደተለመደው ወሳኙን ድርሻ እንዲጫወት” ጠይቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ ከአሜሪካ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ አውሮፓ ህብረት እና እንግሊዝ የተወጣጡ አምባሳደሮች በትግራይ ውስጥ ስለተፈጠሩ ክስተቶች እና አስተዳደሩ ስላጋጠሙት ፈተናዎች ገለፃ ማድረጉን በኤክስ ገጻቸው ገልፀዋል። ውይይቱ ያተኮረው ” እየተባባሰ የመጣውን ሁኔታ እንዴት በተሻለ ሁኔታ ማቆም እንደሚቻል” እና የፕሪቶሪያ ስምምነት ሁሉም ወገኖች ወደ ተጨማሪ አለመረጋጋት “እንዳይመለሱ” ለመከላከል እንዲሰሩ ማረጋገጥ ነው ብለዋል።
በተመሳሳይ መልኩ አረና ትግራይ፣ የትግራይ ነጻነት ፓርቲ እና ባይቶ፤ የትግራይ የፀጥታ ኃይሎች ጠባቂ ተቋም እና የትግራይ ህዝብ ደህንነት ዋስትና መሆን አለባቸው ብለዋል። ይሁን እንጂ “አንድ ቡድን በኃይል ሥልጣን ላይ እንዲደርስ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች በትግራይ ላይ አደጋ ያስከትላሉ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።አስ