ህግ እና ፍትህዜና

ዜና፡ የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር አቶ ታዬ ደንደአ ከቀረቡባቸው ሶስት ክሶች በሁለቱ ነጻ ሲባሉ በአንዱ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30/ 2016 ዓ/ም፦ የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ታዬ ደንደአ ከቀረቡባቸው ሦስት ክሶች መካከል በ1ኛ እና በ2ኛ ክስ ነጻ የተባሉ ሲሆን በ3ኛው ክስ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ፡፡

ብይኑን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሕገ-መንግሥትና በሕገ-መንግሥት ሥርዓት ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት ነው።

በዚህም መሰረት ተከሰውበት በነበረው በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 251/ሐ እና አንቀጽ 257/ሰ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ እና የጦር መሳሪያ አዋጅን መተላለፍ ከሚል ክስ ነጻ ተብለዋል።

በተጨማሪም የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሲሰሩ የሀገርን፣ “የመንግስትና የህዝብን ደህንነት ማስጠበቅ ማረጋገጥ ሲገባቸው ይህን ወደጎን በመተው የሽብር ቡድኖችና የፀረሰላም ኃይሎችን የሚደግፉ ፕሮፖጋንዳ መልዕክቶችን በስማቸው በከፈቱት ማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ ሲያስተላልፉ ነበር” ከሚለው ክስ ነጻ መባላቸው ተገልጿል፡፡

ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ተላልፈዋል የተባሉ የፕሮፓጋንዳ መልዕክቶችን የያዙ የሠነድ ማስረጃዎችን መርምሮ ዛሬ ብይን የሰጠው ፍርድ ቤቱ በዚህም ተመሳሳይነት ያላቸውን ንግግሮችና ጽሑፎች ዐቃቤ ሕግ የተለያየ ክስ አድርጎ 1ኛ እና 2ኛ ብሎ ማቅረቡ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 61ን ያላገናዘበ ነው ብሏል፡፡

ተከሳሽ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ያጋሩትና ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ የሰጡት ቃለ መጠይቅ ሐሳብን የመያዝና የመግለጽ ሕገ-መንግሥታዊ መብትን በመጠቀም ሐሳብን ከመግለጽ ያለፈ፣ የሕዝብን ደኅንነት፣ ሰላምን፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታ እንዲሁም የዜጎችን ነጻነት የሚነካ ሆኖ አላገኘነውም በማለት መከላከል ሳያስፈልግ በ1ኛ እና 2ኛ ክስ በወ/መ/ስ/ሕግ ቁጥር 141 መሰረት በነጻ አሰናብቷቸዋል።

ነገር ግን በ3ኛው ክስ ማለትም ታኅሣስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ከረፋዱ 5 ሠዓት ላይ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በተደረገ ብርበራ አንድ ታጣፊ ክላሽንኮቭ ከሁለት የክላሽንኮቭ ካዝና እና ከ60 ጥይት ጋር ተይዞባቸዋል ተብሎ የቀረበውን ክስ በተመለከተ መሳሪያው መገኘቱ በዐቃቤ ሕግ ማስረጃ የተረጋገጠ መሆኑን በመጥቀስ ፍርድ ቤቱ በወ/መ/ስ/ሕግ ቁጥር 142/1 መሰረት በተከሰሱበት የጦር መሳሪያ አዋጅ 1177/2012 አንቀጽ 4 ንዑስ ቁጥር 1 እና በአንቀጽ 22 ንዑስ ቁጥር 3 የሕግ ድንጋጌ ሥር ክሱን እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ፍርድ ቤቱ ይህን ብይን ያስተላለፈው ክሱ ከደረሳቸው በኋላም ተከሳሹ “የጻፍኩት ጽሑፍ ፕሮፓጋንዳ አይደለም፤ ወንጀል አልፈጸምኩም” ሲሉ የዕምነት ክህደት ቃል ከሰጡ በኋላ፤ ዐቃቤ ሕግ ምስክር እንዲሰማ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የምስክር ጭብጥ በችሎት ካስመዘገበ በኋላ የሁለት ግለሰቦች የምስክር ቃላቸውን ማሰማቱንና ችሎቱ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ተላልፈዋል የተባሉ የፕሮፓጋንዳ መልዕክቶችን የያዙ የሠነድ ማስረጃዎችን መመርመሩን ተከትሎ ነው።

ከብይኑ በኋላም ተከሳሹ እንዲከላከሉ በተበየነበት 3ኛ ክስ የዋስትና መብት ተፈቅዶ በውጭ ሆነው ጉዳዩን ለመከታተል እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ሕግም ተከላከል የተባለበት ድንጋጌ ከ8 ዓመት እስከ 20 ዓመት የሚያስቀጣ ድንጋጌ በመሆኑና የዋስትና ግዴታውን አክብሮ ላይቀርብ ይችላል በማለት የዋስትና መቃወሚያ መከራከሪያ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱ በበኩሉ የዋስትና ጥያቄንው መርምሮ ከሠዓት በኋላ በነበረ ቀጠሮ ተከሳሹ በዋስ ቢወጣ የሕግ ግዴታውን አክብሮ ሊቀርብ አይችልም የሚለውን ግምት በመያዝ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል፡፡

ከዚህ በኋላም ተከሳሹ “አንድ ክላሽንኮቭ ይዟል ተብዬ ዋስትና መከልከሌ ተገቢ አይደለም” የሚል ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱም ብይኑ ከሕግ አንጻር የተሰጠ መሆኑን አስረድቷል፡፡

“በጠበቆቼ ላይ ጫና በማሳደር እንዳይቆሙልኝ ተደርጌያለሁ” በማለት ተከሳሹ አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ ጠበቆቹ መሥራት አልቻልንም በማለት በራሳቸው እንዲያመለክቱ በመግለጽ፤ የመንግሥት ተከላካይ ጠበቃ ለተከሳሹ ሊቆም ይችላል በማለት ገልጿል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ተከላከል በተባሉበት 3ኛ ክስ ላይ የመከላከያ ማስረጃ ለመጠባበቅ ለጥቅምት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ፋና ዘግቧል፡፡

የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ታዬ ደንደኣ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ተከትሎ ታህሳስ 2 ቀን በጸጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

ግንቦት 13 በዋለው ችሎት አቶ ታዬ ያቀረቡትን የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎ ነበር።  ተከሳሹ ያቀረቡትን ‘‘ክሱ ይሻሻልልኝ’’ ጥያቄን የያዘው የክስ መቃወሚያ ውድቅ የተደረገው “ክሱን ለማሻሻል የሚያስችል የህግ አግባብነት የለውም” በሚል መሆኑ ተገልጿልአስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button