ዜና፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከተሞች ዘግናኝ የግድያ ወንጀሎች በተደጋጋሚ እየተፈጸሙ ነው- የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4/2016 ዓ/ም፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዋና ዋና ከተሞች በዜጎች ላይ” ዘግናኝ የግድያ ወንጀሎች” በተደጋጋሚ እየተፈጸሙ መሆናቸዉን የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ገለጸ።

በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ፓርቲው መጋቢት 4/2016 ባወጣው መግለጫ፤ ባለፉፊ ስድስት ወራት በከተሞች የቡድን ዝርፊያ፣ ውንብድና፣ ሰዎችን መሰወር፣ ህጻናት ማገትና አሰቃቂ ግድያዎች እየተበራከቱ ይገኛሉ ሲል ገልጾ፤ አጥፊዎች ለህግ ቀርበው ተጠያቂ አልተደረጉም ብሏል።  

የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፤ በግልገል በለስ ከተማ ሁለት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ዉስጥ አንድ የፖሊስ ከፍተኛ መኮንን፣ አንድ ወጣት የኮሌጅ ተማሪ፣ በፓዌ ከተማ አንድ ከፍተኛ ጠበቃና የህግ አማካሪ በጥይት ተመተዉ ተገድለዋል ብሏል፡፡ በወምበራ ወረዳም አንድ ባለሀብት “በግፍ” ተገድለዋል ሲል ገልጿል፡፡

የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በአሶሳ ከተማ አቅራቢያ ሲስተር ትዕግስት ጥላሁን በተባለች ገለሰብ ላይ “ዘግናኝ ጠለፋና የግድያ” የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን ያስታወቀው ድርጅቱ፤ ተጠርጣርዎች እስከ ዛሬ ድረስ በቁጥጥር ስር አለማዋለቸዉ የዜጎች በሕይወት የመኖር ዋስትና አደጋ ላይ መሆኑን ተገንዝበናል ሲል ገልጿል።  

“ፓርቲያችን ከተለያየ አቅጣጫ  እንደደረሱት መረጃዎች ከሆነ ሲስተር ትዕግስት ጥላሁን ተጠልፋ ከተሰወረችበት የካቲት 16/2016 ዓ.ም ጀምሮ በግፍ ተገድላ ወንዝ ዳር ተጥላ እስከተገኘችበት የካቲት 27/2016 ዓ.ም ድረስ ባሉት ቀናት ፖሊስ ተገብዉን ክትትል ቢያደርግ በሕይወት ማትረፍ የሚቻልበት ዕድል እንደነበረ እናምናለን” ብሏል፡፡

ፓርቲው በመግለጫው፤ የክልሉ መንግስት  በዜጎች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ የግድያ ወንጀሎችን የማስቆም ግዴታ እንዳለበት አሳስቧል። 

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የዜጎችን ሕይወት እየነጠቁ ያሉ ወንጀለኞች ታድነዉ ለሕግ እንድቀርቡ፤ በሕግ ቁጥጥር ስር የዋሉት ደግሞ ተገቢዉን ፍርድ እንዲያገኙ ጠይቋል።

በመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ለሠላም እጅ ያልሰጡ የታጠቁ ኃይሎች ፀብ ጫሪ እንቅስቃሴ አከባቢውን መልሶ ለግጭት የሚጋብዝ በመሆኑ የፀጥታ ኃይሉ ተገቢውን ጥንቃቄ እና እርምጃ እንዲወሰድ እንዲሁም በከማሽ ዞን ሰዳል ወረዳ መነሻቸውን ከሱዳን ያደረጉ በሰላማዊ ዜጎች እና አንድ የፀጥታ አባል ላይ ያደረሱት ግዲያ እና አካል ጉዳት አከባቢው ላይ የፀጥታ ስጋት የደቀነ በመሆኑ መንግስት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ፓርቲው አሳስቧል።አስ

Exit mobile version