ዜና፡ በአማራ ክልል የተፈጠረውን ችግር በጦርነት መፍታት አይቻልም ስንል ለጠ/ሚኒስትር አብይ ነግረናቸዋል ሲሉ ማይክ ሀመር ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 21/2016 ዓ.ም፡- የአሜሪካ የታችኛው ምክር ቤት ኮንግረስ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የአፍሪካ ጉዳዮች ንኡስ ኮሚቴ ‘’በኢትዮጵያ ተስፋ ወይንስ ስጋት፣ የአሜሪካ ፖሊሲ ሁኔታ’’ በሚል ርዕስ ትላንት ሐሙስ ህዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሚመለከታቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናትን ጠርቶ ምስክርነት ሰምቷል።

የኮንግረሱ የአፍሪካ ጉዳዮች ንኡስ ኮሚቴ በነበረው ፕሮግራም የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሀመር እና የዩኤስኤድ የአፍሪካ ረዳት አስተዳደር ቴለር ቤከልማን ተገኝተው ገለጸ የሰጡ ሲሆን ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽም ሰጥተዋል።

በፕሮግራሙ መክፈቻ የኮንግረስ የውጭ ጉዳዮች የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ጆን ጄምስ  በትግራይ ተካሂዶ የነበረው ጦርነት በአማራ እና ኦሮምያ ክልሎች ላይ በመካሄድ ላይ ያለው ግጭት እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀይባህር ላይ የወደብ ተጠቃሚነት ጋር ያደረጉትን ንግግሮች በመጥቀስ የኢትዮጵያ ሁኔታ እጅግ እንደሚያሳስባቸው አስታውቀዋል።

ግጭቶቹ በኢትዮጵያ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ያለውን ስር የሰደደ ልዩነት ያጋለጡ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር የመሰረተችውን የጠበቀ ግንኙነት በማውሳት እና በቅርቡ ብሪክስን መቀላቀሏን በመጥቀስ ፊቷን ከምዕራቡ አለም በማዞር ላይ ብትገኝም ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሬ ለመሸፈን ስትል ብቻ ከእኛ ጋር ግንኙነቷን ጠብቃለች ሲሉ ተችተዋል።

ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር ተሞክሮ የነበረው ድርድር አለመሳካት እና የአማራ ክልል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ለጠረንጴዛ ዙሪያ እንኳ አለመብቃቱ፣ የፕሪቶርያው ስምምነት ሙሉ በሙሉ አለመተግበሩ፣ በትግራዩ ጦርነት ወንጀል የፈጸሙ ፍትህ አለማግኘታቸው ሀገሪቱ በምን ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ማሳያ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

ከፕሪቶርያው ስምምነት ማግስት ጀምሮ የአሜሪካ መንግስት ለተግባራዊነቱ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን በፕሮግራሙ በምስክርነት የታደሙት የሀገሪቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሀመር አስታውቀዋል። በትግራይ ከስምምነቱ በኋላ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የቀነሱ ቢሆንም አሁንም ብዙ ይቀራል፣ የኤርትራ ወታደሮች ከተቆጣጠሯቸው የትግራይ ቦታዎች አልወጡም ብለዋል። የትግራይ ሰራዊት አባላትን ወደ ህብረተሰቡ የመቀላቀል ተግባር መጓተቱን የጠቀሱት ማይክ ሀመር አወዛጋቢ የሆኑት የክልሉ ግዛቶች አለመመለሳቸውንም አስታውቀዋል።

በአማራ እና በኦሮምያ ክልሎች በመካሄድ ላይ ያሉት ግጭቶች ጋር በተያያዘ የጅምላ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ ለመሆኑ አሳማኝ ሪፖርቶች አሉ ሲሉ ገልጸዋል። በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፣ የኢኮኖሚ ጉዳትም አስከትሏል ሲሉ ገልጸዋል። ተፋላሚ ሀይሎች ከሰብአዊ መብት ጥሰታቸው እንዲታቀቡ አሳስበናል ብለዋል። ተፋላሚዎች ሰላማዊ ድርድር የሚያካሂዱ ከሆነ ለማመቻቸት እና ለመደገፍ ዝግጁ ነን ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት አመታት አገሪቱ አጋጥሟት በማያውቀው ሁኔታ የውጭ ምንዛሬ እጥረት አጋጥሟታል ሲሉ ገልጸዋል።

በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በፌደራል መንግስት ወታደሮች መካከል ያለውን ግጭት ለማስቆም የአሜሪካ መንግስት እየጣረ ነውን ተብለው የተጠየቁት ማይክ ሃመር አወን የሚል ምላሽ ሰጥተው ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ከጠ/ሚኒስትሩ እና ከከፍተኛ አማካሪዎቻቸው ጋር በተገናኘንበት ወቅት በአማራ ክልል ያለውን ችግር በወታደራዊ መንገድ ምንም አይነት መፍትሔ ማምጣት እንደማይቻል ገልጸንላቸዋል፣ ሰላማዊ ድርድር እንዲጀምሩ መክረናቸዋል ብለዋል።

በተደጋጋሚ ተፋላሚ ሀይሎቹ በሰላማዊ ዜጎችን ከመጎዳት እንዲጠብቁ አሳስበናል። አሜሪካ የዲፕሎማሲ መንገዶቿን ተጠቅማ ክልሉ ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጣ ጥረት ታደርጋለች ብለዋል።

የዩኤስኤድ የአፍሪካ ረዳት አስተዳደር ቴለር ቤከልማን በበኩላቸው ተቋርጦ የነበረውን የምግበ እረዳታ ለማስጀመር ያስቻሉ ማሻሻያዎች እርዳታዎቹ ለታለመለት ግብ እንደሚውሉ የሚያደርጉ መሆናቸውነ አስታውቀዋል። የእርዳታ ምግብ አቅርቦቱ ለታለመለት አላማ እየዋለ አለመሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎች ከተገኙ ግን ለማቆም እድሚገደዱም ጠቁመዋል። አስ

Exit mobile version