ዜና፡ በፀጥታ ችግር የተነሳ በአማራ ክልል ባሉ ሆስፒታሎች የመድኃኒትና ህክምና አቅርቦት እጥረት መከሰቱን የክልሉ ጤና ባለ ሙያዎች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 12/ 2016 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል በርካታ እካባቢዎች እየተካሄድ ባለው ግጭት ምክንያት በሆስፒታሎች ላይ ከፍተኛ የመድኃኒት እና ሌሎች የህክምና አቅርቦቶች እጥረት መከሰቱን የክልሉ ጤና ባለ ሙያዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ፡፡

የደብረ ማርቆስ አጠቃላይ ሆስፒታል ኃላፊ አንዱአለም ገረመው፣ በተለይ እንደ ስኳር በሽታ ያሉ መድኃኒቶች እጥረት አሳሳቢ መሆኑን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። የላብራቶሪ መመርመሪያ እጥረት የዶክተሮች ህሙማንን በአግባቡ የመከታተል እና የማከም አቅማቸው ላይ እንቅፋት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሃላፊው እጥረቱ የተከሰተው በአቅራቢያ ባሉ ወረዳዎች በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ከደብረ ማርቆስ አዲስ አበባ  ያለው መንገድ በመዘጋቱ ነው ብለዋል። በተጨማሪም የፌዴራልም ሆነ የክልሉ መንግስት በቂ አቅርቦት ባለማድረጋቸው በደብረ ማርቆስና በአካባቢው የሚገኙ ዘጠኝ ሆስፒታሎችም ተመሳሳይ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዋግ ኀምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ጤና ቢሮ ኃላፊ አስፋ ነጋሽ በዞኑ የመደኃኒት እጥረት መኖሩን ለአዲስ ስታንዳርድ አርጋግጠዋል። በህክምና አቅርቦቶች ላይ ከፍተኛ ልዩነት መኖሩን እና ይህም እየተከሰቱ ባሉ ግጭቶች ሳቢያ በመንገዶች መዝጋት መባባሱን ተናግረዋል። በተለይ በሃኪም የታዘዙ ተጨማሪ ሟሟያ  ምግብ ፕሮግራሞች ላይ ጥገኛ የሆኑ ሴቶች እና ህጻናት ላይ ተጽኖ እያደረሰ መሆኑን አብራርተዋል። 

መንገዶች በመዘጋታቸው ዞኑ የሟሟያ  ምግቦችን ከጎንደር እና ኮምቦልቻ ከተማ ማግኘት አልቻለም ብለዋል። ጤና ቢሮው፣ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ለነዋሪዎች የጤና ፍላጎቶችን ለመጠበቅ ኃላፊነቱን ለመወጣት እየሰራ ነው ሲሉ ኃላፊው አክለዋል ።

ሌላኛው መንገዶች መዘጋት ያሰከተለውን የህክምና ቀዉስ ያስረዱት የዳባት ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ሰለሞን ለገሰ ናቸው፡፡ እንደ አስም እና የደም ግፊት ያሉ በሽታዎችን ለመቆጣጠር የመድኃኒት እጥረት መኖሩን ጠቁመዋል። አገር ውስጥ ካሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተወሰነ ዕርዳታ ቢገኝም፣ አስፈላጊ የሆኑ የሕክምና ቁሳቁሶችን በማግኘት ረገድ ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ድርጅት መድኃኒቶችን ወደ ተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች ለማሰራጨት፣ ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ የተነሳ ዕንቅፋት እንደፈጠረበት አስታወቋል፡፡ በድርጅቱ የመድኃኒት ክምችት እና ስርጭት ዘርፍ ምክትል ዲሬክተር አቶ ታሪኩ ለአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ በሰጡት አስታየት፣ በክልሉ የጸጥታ ችግር መደፍረስ ከታየበት ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ፣ በአውሮፕላን የካርጎ አገልግሎት ጭነት፣ ወደ ባሕር ዳር፣ ደሴ እና ጎንደር ከተሞች መድኃኒት ሲላክ እንደቆየ ጠቅሰው ወደ ዞኖች እና ወረዳዎች ለማሰራጨት ግን፣ በጸጥታው ችግር የተነሳ አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የደሴ ቅርንጫፍ ሃላፊ የሆኑት እሸቴ ሹሚ ወደ አማራ ክልል ወረዳዎች መድኃኒት እየደረሰ አይደለም የሚለውን መረጃ ውድቅ አድርገዋል። አቶ እሸቴ ከግጭት ጋር በተያያዘ ጊዚያዊ መዘግየቶች መኖራቸውን ቢያመኑም፣ አሁንም ወሳኝ የሆኑ አቅርቦቶች ወደ ዞኖች እንደሚደርሱ ገልጸዋል።

በአማራ ክልል እየተካሄድ ያለው ግጭት ሌሎች ወሳኝ አቅርቦቶችንም እያስተጓጎለ ይገኛል። ጥቅምት 6 ቀን  የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የስራ ኃላፊ አስቸኳይ የምግብ አቅርቦቶችን የጫነ ተሽከርካሪ በፀጥታ ችግር ምክንያት በህርዳር እንዲቆይ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ የማህበሩ የሰብአዊ ዲፕሎማሲ እና የግንኙነት ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ መስፍን ደረጀ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት ግጭቶች በተደጋጋሚ መንገዶች እነዲዘጉ በማድርግ የሰበዓዊ ዕርዳታ አቅርቦቶች ወደ በአማራ ክልል ከተሞች እንዳይገቡ እያደረገ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከጁቡቲ ወደብ ማጓጓዝ የተጀመረውን የአፈር ማዳበሪያ ስርጭትንም አስተጓጎሏል። የክልሉ ግብርና ቢሮ “ፀረ ሰላም ሀይሎች” የአፈር ማዳበሪያ ላይ ዝርፊያ እየፈጸሙና በጊዜውና በወቅቱ ለገበሬዎች እንዳይደርስ  እያደረጉ መሆኑን አስታውቋል፡፡አስ

Exit mobile version