ዜና፡ አሜሪካ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ እና ግብጽን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማስማማት አሁንም ዝግጁ ነኝ ብላለች – የግብጽ ሚዲያ

የግድቡ የሲቪል ሥራ 98 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራው 78 በመቶ መድረሱን ኢትዮጵያ አስታውቃለች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27/2016 ዓ.ም፡- አሜሪካ ኢትዮጵያ እና ግብጽ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማስማማት አሁንም ዝግጁ ናት ሲሉ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር እንደገለጹለት የግብጹ አልምስር አልዮም ጋዜጣ አስነብቧል።

አሜሪካ ግብጽ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ከስምምነት ላይ እንዲደርሱ ለማድረግ ቁርጠኛ ናት ሲሉ ቃል አቀባዩ ገልጸውልኛል ያለው ጋዜጣው ግድቡን በማስተዳር፣ አጠቃቀም እና ውሃ አቅርቦት ዙሪያ ሀገራቱ የአፍሪካ ቀንድን ሰላም እና መረጋጋት ባስጠበቀ መልኩ እንዲወያዩ ለማድረግ ዝግጁ ነን ማለታቸውንም አስታውቋል።

የህዳሴው ግድብ አፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋት ላይ ያለውን ተጽእኖ የመፍጠር እድል ዋሽንግተን እንዴት ታየዋለች? በአፍሪካ ቀንድ አሉታዊ ውጤት እንዳያስከትልና ለማለሳለስ ምን አይነት እርመጃ ለመውሰድ ሀሳብ አላት? ሲል ለቃል አቀባዩ ጥያቄ ማቅረቡን ያስነበበው ጋዜጣው ቃል አቀባዩ ቀጥታዊ ምላሽ ሳይሰጡ በግድቡ ዙሪያ ዩናይትድ ስቴት በግድቡ ዙሪያ መፍትሔ ለማምጣት የሚደረግ የዲፕሎማሲ ጥረትን ለማገዝ ዝግጁ ነች በማለት እንደገለጹለት አስታውቋል።

ጋዜጣው ያነጋገራቸው የቀድሞ የአሜሪካን አምባሳደር በኢትዮጵያ ቲቦር ናጌ በበኩላቸው አሜሪካ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ እና ግብጽ መፍትሔ እንዲያበጁለት ትሻለች ሲሉ እንደገለጹለት አስታውቆ ለዚህም ዋነኛ ምክንያት ግብጽ በመካከለኛው ምስራቅ የአሜሪካ አስፈላጊ አጋሯ ናት፤ በአፍሪካ ቀንድ ተጽእኖዋ ከአመት አመት እየጨመረ የመጣው ኢትዮጵያ ደግሞ ለአሜሪካ ታስፈልጋታለች ማለታቸውን አስነብቧል።

ዋሽንግተን ጉዳዩ በሁለቱ ሀገራት እንዲፈታ ነው የምትፈልገው ማለታቸውንም አካቷል።

የባይደን አስተዳደር በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ፍላጎት እንዳለው ቢታወቅም አለም በተለያዩ አንገብጋቢ አጀንዳዎች በመጠመዱ ሊሰጡት የሚችሉት ትኩረት የተገደበ ነው ሲሉ ቲቦር ናጌ እንደገለጹለት ጋዜጣው በዘገባው አስነብቧል።

በተያያዘ ዜና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አፈፃፀም 95 በመቶ መድረሱን የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል ከዚህም ውስጥ የሲቪል ሥራው 98 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮሜካኒካል ሥራው 78 በመቶ መድረሱን አስታውቋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መሠረት ድንጋይ የተጣለበት 13ኛ ዓመት “በኅብረት ችለናል!” በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል ያለው ጽ/ቤቱ ባለፉት 13 ዓመታት 18 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ከሕዝብ ተሳትፎ ተሰብስቧል ሲሉ የግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍቅርተ ታምር በሰጡት መግለጫ መናገራቸውንም አመላክቷል።

Exit mobile version