ዜና፡ ኢጋድ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ሁኔታ በጥንቃቄ እየተከታተለው እንደሚገኝ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 24/2016 .ም፡ ኢጋድ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ሁኔታ በጥንቃቄ እየተከታተለው እንደሚገኝ ገልጿል፤ በቀጠናው ሰላም ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ እንደሚገነዘብ አስታውቋል።  

ዋና ጸሀፊው ወርቅነህ ገበየሁ በቅርቡ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረው ጉዳይ እንዳሳሰባቸው ጠቁመዋል።  

ኢጋድ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረው ሁኔታ በጥንቃቄ እየተከታተለው መሆኑን እና በቀጠናው ሰላም ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ እንደሚገነዘብ ከመግለጽ ባለፈ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስለተፈራረሙት መግባቢያ ሰነዱ ያለው ነገር የለም።

በተጨማሪም ዋና ጸሃፊው ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ የኢጋድ አባል ሀገራት  መሪዎች ሁኔታውን በርጋታ እንዲመለከቱት እና ሁለቱ እህተማማች ሀገራት በሰላማዊ መንገድ በመተባበር መፍትሄ እንዲሰጡት አሳስቧል።

በተመሳሳይ በትላንትናው ዕለት አመሻሽ ላይ የአዉሮፓ ህብረት ባወጣው መግለጫ የሶማሊያ ሉዓላዊነት ሊከበር ይገባል ሲል አሳስቧል፤ የሶማሊያ የድንበር ወሰን፣ አንድነቷ እና የሀገሪቱ ክብር ሊጠበቅ ይገባል ብሏል።

ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባህር በር ለመስጠት እና በምትኩ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ እውቅና ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት በጠ/ሚኒስትር አቢይ አሕመድ እና የሶማሌላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አብዲ መካከል በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰንድ መፈረሙ ይታወቃል።

እንደ ሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መግለጫ ከሆነ የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባህር በር ለመስጠት እና በምትኩ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ እውቅና ለመስጠት የሚያስችል ነው።

የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ለአዲስ ስታንዳርድ የላከው መገለጫ እንደሚያመላክተው የተፈረመው ታሪካዊ ስምምነት ኢትዮጵያ ለባህር ሀይሏ የሚሆን ቦታ ከሶማሊላንድ የሚያስገኝላት ሲሆን በተመሳሳይ ማንም ሀገር እውቅና ሰጥቷት የማታውቀው ሶማሊላንድ ደግሞ ከኢትዮጵያ ሙሉ እውቅና እንድታገኝ ያደርጋታል ብሏል። አስ

Exit mobile version