ዜና፡ ከአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ አሁንም የጅምላ እስሮች እየተፈጸሙ ነው ሲል ኢሰመጉ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 27/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ ከአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ አሁንም ድርስ የጅምላ እስሮች እየተፈጸሙ ነው ሲል ገለጸ። ኢሰመጉ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና በአማራ ክልል እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በአስቸኳይ ሊቆሙ ይገባል ሲል ባወጣው መግለጫ በአዲስ አበባ እየተፈጸሙ ያሉት እነዚህ እስሮች የህግ ስነስርዓትን ያልተከተሉ እና አንዳንዶቹም አስገድዶ የመሰወር ባህሪ ያላቸው ናቸው ብሏል።

በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በአዲስ አበባ ፖሊስና በፌደራል ፖሊስ አንዳንዶቹም የሰሌዳ ቁጥር የሌላቸውን መኪናዎች ጭምር በመጠቀም ከተያዙ በኋላ ወደ አፋር ክልል አዋሽ አርባ እንደሚወሰዱ ኢሰመጉ ከታሳሪ ቤተሰቦች መረጃ ማግኘቱን በመግለጫው አመላክቷል።

ኢሰመጉ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ለተለያዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በደብዳቤ ማብራሪያ ቢጠይቅም ምላሽ አለማግኘቱን አስታውቋል።

ከእስር ሁኔታው ጋር በተያያዘ ኢሰመጉ በመግለጫው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር ካሳ ተሻገር ከተያዙበት ጊዜ አንስቶ ያለመከሰስ መብታቸው አለመነሳቱን እና ያሉበት ቦታም በግልጽ ለማወቅ አለመቻሉን አስታውቋል።

የአልፋ ሚዲያ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነው ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ቤተሰቦቹ የት እንዳለ እንደማያውቁ ያመላከተው መግለጫው ጋዜጠኛ አባይ ዘውዱን አስመልክቶ በተሰበሰበ መረጃ መሰረት ጋዜጠኛው በ15/12/2015 ዓ.ም ወደ አዋሽ አርባ መወሰዱን ቤተሰቦች ከተለያዩ ምንጮች እንደሰሙ ነገር ግን ማረጋገጥ እንዳልቻሉ ጠቁሟል።

በተመሳሳይ ኢሰመጉ በመግለጫው በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ማለትም ባህርዳር፣ መራዊ፣ ደምበጫ፣ አማኑኤል፣ ሉማሜ፣ ደብረማርቆስ፣ ፍኖተሰላም፣ ብቸና፣ ደብረታቦር፣ ወረታ፣ አዲስ ዘመን እና ሌሎችም አካባቢዎች ላይ ግድያ፣እገታ ፣እስር፣ ዘረፋ እንዲሁም በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃት እንደቀጠለ መሆኑን አስታውቋል።

አዲስ በተመሰረተው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከመመስረቱ ጊዜ አንስቶ የሰብዓዊ የመብት ጥሰቶች እየተስተዋሉ እንደሚገኙ ኢሰመጉ በመግለጫው አስታውቋል።

ኢሰመጉ በመግለጫው ባቀረበው ጥሪ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚፈጸሙ የጅምላ እስሮች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ በእስር ላይ ያሉ ሰዎች ፍርድ ቤት አንዲቀርቡ፣ የሚደረጉ እስሮች ተገቢውን የህግ ሰነስርዓት እንዲከተሉ እና የታሰሩ ሰዎች ያሉበት ስፍራ ይፋ እንዲደረግ ጠይቋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያለው ውጥረት እየተባባሰ ሳይሄድ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ አሳስቧል።

የፌደራልና የአማራ ክልል መንግስታት በአማራ ክልል በንጹሀን ላይ እየደረሰ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በቂ ትኩረት በመስጠት የሰዎች በህይወት የመኖር መብትን እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ ጠይቋል።

Exit mobile version