ዜና፡ የመንግስታቱ ድርጅት ያቋቋመው መርማሪ ቡድን በኢትዮጵያ የስራ ግዜ ሳይራዘም ቀረ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24/2016 ዓ.ም፡- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን እንዲመረምር ያቋቋመውን የባለሞያዎች ቡድን የምርመራ ግዜ እንዲያራዝም በተደጋጋሚ በበርካታ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ውትወታ እና ጥሪ ሲቀርብ እንደነበር ይታወቃል።

የመርማሪ ቡድኑ የስራ ግዜን ሳይራዘም የቀረው ከየትኛውም #የአለም ክፍል ለመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ቡድኑ እንዲራዘም የሚጠይቅ የቀረበ ረቂቅ ሀሳብ ባለመኖሩ መሆኑ ታውቋል።

የሂዩማን ራይት ዎች የአውሮፓ ዳይሬክተር የሆኑት ፊሊፕ ደም ህብረቱ የመርማሪ ቡድኑ የስራ ግዜ እንዲራዘም ረቂቅ ሃሳብ አለማቅረቡን አጥብቀው ኮንነዋል፤ የአውሮፓ ህብረት በህብረቱ የሰፈሩ ዋነኛ መርሆችን በሚጻረር መልኩ ተንቀሳቅሷል፣ የመንግስታቱ ድርጅትን ቁልፍ ምርመራ እንዲቀበር የመሪነት ሚና ተጯውቷል ሲሉ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

ጉዳዩን በቅርበት ከሚከታተሉ ሰዎች መካከል የሆኑ እና የአዲስ ስታንዳርድ ታማኝ ምንጮች እንዳደረሱን መረጃ ከሆነ ምንም እንኳ የአውሮፓ ህብረት የመርማሪ ቡድኑ የስራ ግዜ እንዲራዘም የሚያስችል ረቂቅ ሃሳብ ባያቀርብም የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ሃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ለህብረቱ አባል ሀገራት በጻፉት የውስጥ ደብዳቤ የመንግስታቱ ድርጅት የመርማሪ ቡድን በኢትዮጵያ የስራ ግዜ ባይራዘምም የህብረቱ አባል ሀገራት ቡድኑ ካቀረበው ሪፖርት የተነሳ የኢትዮጵያ መንግስትን አሁንም የሰብአዊ መብት አያያዙን እየተከታተልነው መሆኑን እና አሳማኝ የሽግግር ፍትህ ማካሄድ እንደሚገባው ማስገንዘብ ይጠበቅብናል ማለታቸውን ገልጸዋል።

የመርማሪ ቡድኑ እንዲቋቋም የውሳኔ ሃሳብ አቅርቦ ያጸደቀው አውሮፓ ኅብረት ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርብ ሂዩማን ራይት ወችን ጨምሮ በርካታ ተቋማት ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡለት እንደነበር ይታወሳል። መስከረም 18 ቀን 2016 . አዲስ ስታንዳርድ ባስነበበው ዘገባ የቡድኑ የምርመራ ግዜ እንዲያራዝም ሂዩማን ራይት ዎች የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ሚና እንደሚጠበቅበትም ባወጣው መግለጫ ማመለከቱ በወቅቱ ተዘግቧል። ተበዳዮችም ሆኑ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች የሀገሪቱ  የፍትህ ተቋማት ፍትህ ያሰፍናሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪው ተቋም በመግለጫው አስታውቆ ነበር። በወቅቱ ሂዩማን ራይት ዎች የአለም አቀፉ የመርማሪዎች ቡድን እንዲቋቋም ከፍተኛ ሚና የተጫወተው የአውሮፓ ህብረት አሁንም የስራ ግዜው እንዲራዘም ረቂቅ ሃሳብ በማዘጋጀት ረገድ የመሪነት ሚና እንዲጫወት መጠየቁ ይታወሳል።   

መርማሪ ቡድኑ ረቂቅ የመፍትሔ ሃሳብ ለህብረቱ ጉባኤ ለማቅረብ አንድ ሳምንት እየቀረበውም ቢሆን የአውሮፓ ህብረት ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንደማይታይበት በመግለጽ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪው ተቋም ህብረቱን በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ተችቷል።

በሌላ በኩል ጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም በአለማችን ከፍተኛ ተጽኖ ፈጣሪ የሆኑ ታላላቅ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በጋራ በመሆን የመንግስታቱ ድርጅት በኢትዮጵያ የሚያካሂደውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ እንዲካሂድ ያቋቋመውን ቡድን ተልዕኮን ለተጨማሪ አንድ አመት እንዲያራዝም መጠየቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል። ጥያቄውን ያቀረቡት አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂዩማን ራይት ዎች፣ ኦክስፋም እና የአለም የሰላም ፋውንዴሽንን ጨምሮ 63 የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በጋራ በጻፉት ደብዳቤ እንደነበር በዘገባው ተጠቅሷል።

የአለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ኤክስፐርቶች በኢትዮጵያ (ICHREE) ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት በኢትዮጵያ አሁንም የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እንደቀጠለ ነው ሲል መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል። በሀገሪቱ ሰላም ሰፍኗል ለማለት አስቸጋሪ ነው ሲል ቡድኑ በሪፖርቱ አስጠንቅቋል። 21 ገጽ ባለው ሪፖርቱ እንደተገለጸው በጦርነቱ የተሳተፉ ሁሉም አካላት ጦርነቱ ማግስት ጀምሮ ግፍ ፈጽመዋል ብሏል። ከተዘረዘሩት ግፎች መካከልም ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ማስራብ፣ የትምህርት እና የጤና ተቋማት ውድመት፣ ማፈናቀል እና የዘፈቀደ እስር  ይገኙበታል። አስ

Exit mobile version