ዜና፡ የአፍሪካ ህብረት እና የመንግስታቱ ድርጅት አባል ሀገራት የኢትዮጵያን እና የሶማሊላንድን ስምምነት እንዲያወግዙ ሶማሊያ ጠቀች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4/2016 ዓ.ም፡- የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትላንት የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራት ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የደረሱትን የመግባቢያ ሰነድ እንዲያወግዙ ጠየቀ።

ሶማሊላንድ በበኩሏ ተቀባይነት የለውም ስትል ተችታለች።

ስምምነቱ ህገወጥ ነው ሲል በድጋሚ የገለጸው የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ የሶማሊያን ሉዐላዊነት እና ግዛታዊ አንደነት የጣሰ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ ተግባር ከብዙ አስርት አመታት በኋላ ቀጠናው ለመረጋጋት እና ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲል መግለጫው አትቷል።

እንደ አፍሪካ ህብረት መቀመጫነቷ ህብረቱ የተመሰረተለትን የአህጉሩን ሀገራት አንድነት፣ ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት ማስጠበቅ መርህ ከማስከበር ይልቅ በመጣስ የህብረቱን ህልውና ስጋት ላይ የሚጥል ተግባር ፈጽማለች ብሏል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድ፣ አለምአቀፉ ማህበረሰብ ያወደሰውን እና ሀገራችንን ለማረጋጋት እየወሰድነው ያለው እርምጃ ያስመዘገበውን ለውጥ ለማጠልሸት ያለመ ነው ሲል የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ኮንኗል።

ሶማሊያ ባለፉት ሁለት አመታት እየወሰደችው ባለው ጸረ ሽብርተኝነት ዘመቻ በርካታ በሽብረ ቡድኑ ስር የነበሩ ግዛቶችን ማስለቀቁን ያስታወቀው መግለጫው ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የተፈራረሙት ስምምነት ግን ለአልሸባብ ወርቃማ እድል ፈጥሮለታል፣ አሳዛኝ በሆነ መልኩ ያገኘነውን ድል ሊቀለብስ በሚያስችል ሁኔታ እየተጠቀመበት ይገኛል ብሏል።

በዚህም መሰረት የአፍሪካ ህብረት እና የመንግስታቱ ድርጅት አባል ሀገራት በመርህ ላይ ተመስርተው የኢትዮጵያን ተግባር በማውገዝ አቋማቸውን እንዲያንጸባርቁ ጠይቋል።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን መግለጫ ተከትሎ የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ እና አለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ሙሉ በሙሉ እንደማይቀበለው አስታውቋል። ሶማሊላንድ ነጻ እና እራሷን የምታስተዳድር ሉዐላዊ ሀገር ናት ሲል የገለጸው የሶማሊላንድ መግለጫ ሀገሪቱን በምርጫ አሸንፎ የሚያስተዳድረው አካል ማንኛውንም አለም አቀፍ ስምምነት በትብብር መንፈስ የመፈራረም ሙሉ መብት አለው ሲል አስታውቋል።

ሶማሊላንድ በሶማሊያ የሚወጣ ማንኛውመ ጋዜጣዊ መግለጫ አይመለከታትም፣ በጋዜጣዊ መግለጫው የሶማሊላንድ ጉዳይ የሚነሳው ሆን ተብሎ ለማታለል ነው ብሏል።

የሶማሊላንድ መንግስት የሀገሪቱን ነጻነት በሰላማዊ መንገድ ለማግኘት ጥረት ያደርጋል እንዲሁም አለመ አቀፍ እውቅናን ለማግኘት ይጥራል ሲል አመላክቷል።

Exit mobile version