ዜና: 1500 የሚጠጉ የሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን ተፈናቃዮች ወደቀያቸው መመለሳቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24/2016 ዓ.ም፡- በትግራይ ክልል ከሰሜን ምዕራብ ዞን ጸለምት ወረዳ ተፈናቅለው የነበሩ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው መመለስ መጀመራቸው ተገለጸ። በጥቅምት 2014 ዓ.ም በፕሪቶሪያ የተደረሰው ስምምነት መሰረት ተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል ተብሏል።

“ምንም እንኳ በርካታ መሰናክሎች ቢያጋጥሙንም 1456 ነዋሪዎችን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ አድርገናል” ሲሉ የተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለማስመለሰ በተዋቀረው ኮሚቴ የማጓጓዣ ጉዳዮች አስተባበሪ የሆኑት ታደለ መንግስቱ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

አቶ ታደለ መንግስቱ እንዳረጋገጡት የወረዳዋ አራት ቀበሌዎች ማይ አይኒ፣ ማይ አንበሳ፣ መድሃኒአለም እና ውኽዳት ነዋሪዎች ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል።

ማይጸብሪን ጨምሮ ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ተጨማሪ የወረዳዋ ስድስት ቀበሌ ነዋሪዎችን ወደ ቤታቸው ለመመለስ እቅድ የነበረ ቢሆንም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰአት ድረስ ወደ ቀያቸው አለመመለሳቸውን ለማወቅ ተችሏል።

“ አብዘሃኛዎቹ ወደ ቀያቸው ለመመለስ ዝግጅት እያደረጉ ያሉት በወጣትነት እድሜ ክልል ያሉ ናቸው፣ ወደ ቤታቸው ተመልሰው ቤቶቻቸውን በማሰናዳት ቤተሰቦቻቸው እንስኪመለሱ በመጓጓት ላይ ያሉ ናቸው” ሲሉ ታደለ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

እንደ አቶ ታደለ ገለጻ፣ “የተወሰኑ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለሳቸው ትንሽ ተስፋ ቢፈጥርም፣ ከሰሜን ምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው 80ሺ ይደርሳል” ብለዋል፤ ከዚህ አንጻር ቁጥሩ ትንሽ ነው ሲሉ አስታውቀዋል። “ወደ ወረዳዋ በመጀመሪያው ዙር ከ8ሺ 500 እስከ 10ሺ የሚደርሱ ተፈናቃዮች ይመለሳሉ” ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ጠቁመዋል።

አብዘሃኛዎቹ የክልሉ ተፈናቃዮች ለመንግስት እያቀረቡት ከሚገኙ ጥያቄዎች መካከል የጸጥታ እና ደህንነት ሁኔታው እንደሚያሳስባቸው፣ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ መሰረታዊ ነገሮች እንዲሟሉላቸው አለመደረጉ እና በመልሶ መቋቋም ስለሚያጋጥማቸው ተግዳሮት ይገኙበታል።

“ወደ ቀያቸው ለሚመለሱ ተፈናቃዮች የአንድ ወር ቀለብ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እና በመንግስታዊ ባልሆኑ ረድኤት ድርጅቶች እንደተሰጣቸው” አቶ ታደለ አስታውቀዋል።

በአከባቢው የነበሩ የአማራ ክልል መስተዳድር አካላት ተፈናቃዮቹ ከመመለሳቸው ሶስት ቀናት በፊት አከባቢውን ለቀው መውጣታቸውን እና በአሁኑ ሰአት አከባቢው በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር መሆኑን አቶ ታደለ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

የጸለምት አከባቢ ነዋሪዎች ተፈናቃዮቹ ሲመለሱ ደማቅ አቀባበል ቢያደርጉላቸውም ተመላሾቹ አሁንም ስጋት እንደሚሰማቸው የገለጹልን ስማቸው ለደህንነታቸው ሲሉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ እና ከአከባቢው ተፈናቅለው ሶስት አመታት በመጠለያ መኖራቸው የነገሩን ተመላሽ የስጋታቸው ዋነኛ መነሻ በአከባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል። “የተዘበራረቀ ስሜት ነው የሚሰማኝ” ያሉን ተመላሹ “ወደ ቤቴ በመመለሴ ከፍተኛ ደስታ ቢሰማችም የደህንነቴ ሁኔታ ግን ያስጨንቀኛል” ሲሉ ስሜታቸውን አጋርተውናል።

የተመላሾች ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ታደለ መንግስቱ ስጋቶቹ መኖራቸው አምነዋል። “ተመላሾች አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ለቀው ያልወጡ የአማራ ታጣቂዎች ትጥቅ ፈትተው ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ስጋት አድሮባቸዋል” ሲል ገልጸዋል። “ወደ ቀያቸው በመመለሳቸው ደስታ ባሻገር የፈራረሱት ቤቶቻቸው እና በሌሎች መጻኢ ፈተናዎች ዙሪያ ስጋት አላቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ሚያዚያ ወር መጨረሻ ሳምንት በሰጡት መግለጫ የአማራ ክልል ይገባኛል በሚላቸው እና የትግራይን ጦርነት ተከትሎ ክልሉ ጠቅልሎ እንደ አዲስ ባዋቀራቸው የደቡብ ትግራይ እና ጸለምቲ ወረዳዎች አስተዳደሮች እንደሚፈርሱ እና ተፈናቃዮች እንዲመለሱ እስከ ግንቦት 30/2016 ዓ.ም የጊዜ ሰሌዳ ስምምነት ላይ መደረሱን መግለጻቸው ይታወሳል።

በተጨማሪም በአማራ ክልል በኩል ወልቃይት ተብሎ በሚጠራው ምዕራብ ትግራይ እንደ አዲስ የተቋቋመው አስተዳደር እስከ ሰኔ 30 ባለው ጊዜ ይፈርሳል ብለዋል።

በዚህም ውይይት ላይ ትጥቅ መፍታትን አስመልክቶ የትኞቹ አስተዳዳራዊ መዋቅሮች መፍረስ እንዳለባቸው እና የተፈናቀሉ ዜጎች እንደሚመለሱ ዝርዝር እቅድ መውጣቱን፣ ይህንንም የሚቆጣጠረው እና የሚያረጋግጠው የአፍሪካ ኅብረት የስምምነት ክትትል አረጋጋጭ እና አስከባሪ ኮሚቴ እንደሚሆን መናገራቸው ይታወሳል። አስ

Exit mobile version