ዜናቢዝነስ

ዜና፡ በሰዓት 150 ቶን ከሰል የማምረት አቅም ያለው የድንጋይ ከሰል ማጣሪያ ፋብሪካ በቅርቡ ስራ እንደሚጀምር ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 21/2016 ዓ.ም፡- በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ በ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እየተገነባ የሚገኘው የድንጋይ ከሰል ማምረቻ ፋብሪካ ከሁለት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሥራ እንደሚጀምር ተገለጸ።

በዞኑ የከሰል ማዕድን ክምችት በከፍተኛ መጠን የሚገኝ በመሆኑ ይህንን የከሰል ማዕድን አልምቶ ሀገርን እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ መጥቀም ያስፈልጋል ሲሉ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ እንደገለጹለት ኢፕድ ዘግቧል።

ፋብሪካው በተለይ ከውጭ የሚገቡ የታጠበ የድንጋይ ከሰል ምርትን በሀገር ውስጥ ለመተካት ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ሲሉ ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል ያለው ዘገባው የውጭ ምንዛሪ ዕጥረትን ለመቅረፍም የራሱ አስተዋፅዖ አለው ማለታቸውንም አካቷል።

ኢቲ ማይኒንግ የተሰኘው ፋብሪካው እስካሁን አራት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት እና ወደ ሙከራ ትግበራ እየገባ እንደሚገኝ አስተዳዳሪው ገልጸዋል ያለው ዘገባው የኢቲ ማይኒንግ ድርጅት ተወካይ ወንድሙ ምትኩ በበኩላቸው ፋብሪካው የመጨረሻ አስፈላጊ የሚባሉት ነገሮች እየተገጠሙለት ይገኛል፣ በመገባደድ ላይም ነው ማለታቸውን ጠቁሟል።

ከሁለት ዓመት በፊት ግንባታው የተጀመረው ፋብሪካው በአሁኑ ጊዜ አጠቃላይ ሥራው እየተጠናቀቀ በመሆኑ በፋብሪካው የሚሠሩ ቋሚ ሠራተኞች ሥልጠና እየተሰጠ ነው፣ የሙከራ ሥራዎች ከተሠሩ በኋላ ከሁለት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተመርቆ ሥራ ይጀምራል ማለታቸውን አመላክቷል።

ኢትዮጵያ በቂ የከሰል ማዕድን እያላት ከደቡብ አፍሪካ በውጭ ምንዛሪ የታጠበ ከሰል ገዝታ እንደምታስገባ እና በተለይ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በዚህ ምክንያት ለከፍተኛ ወጪ መዳረጋቸውን አቶ ወንድሙ ገልጸዋል ያለው የፕሬስ ዘገባ ፋብሪካው በኢትዮጵያ የሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን የታጠበ ከሰል ፍላጎትን 75 በመቶ የመሸፈን አቅም ያለው ነው ማለታቸውን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ የታጠበ ከሰል ፍላጎት ሀገሪቱ በዓመት በአማካይ 400 ሚሊዮን ዶላር እያሳጣት ይገኛል ሲሉ የፋብሪካው ፕሮጀክት ማናጀር ኢንጅነር በላይ መግለጻቸውን ያስነበበው ፕሬስ ኢቲ ማይንግ ፋብሪካ ሲጠናቀቅ ይህን ወጪ ማዳን ያስችላል ማለታቸውን አመላክቷል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button