ዜናፖለቲካ

ዜና፡ በኢጋድ አሸማጋይነት በሱዳን ተቀናቃኝ ሀይሎች መካከል ሊደረግ የነበረው ውይይት ተራዘመ፣ የፈጥኖ ደራሹ ሀይል መሪ ጄነራል ሀምዳን ደጋሎ አዲስ አበባ ገብተዋል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 18/2016 .ም፡ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሰራዊት አዛዥ ጀነራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሃሜቲ) በዛሬው ዕለት ታህሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ገብተዋል።

ጀነራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሃሜቲ) አዲስ አበባ ሲደርሱም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አቀባበል እንዳደረጉላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒቴር አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ እና ከልዑካን ቡድናቸው ጋር በሱዳን ሰላም እና መረጋጋት ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል። 

ጠ/ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ “በሱዳን ሰላም እና መረጋጋትን ማስፈን በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ለማድረግ ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ እና የልዑካን ቡድናቸውን ተቀብያለሁ” ብለዋል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ አዲስ አበባ የተገኙት ተጠባቂ የነበረውና በኢጋድ አሸማጋይነት በሱዳን ተቀናቃኝ ሀይሎች መካከል ሊደረግ የነበረው ውይይት መራዘሙን ተከትሎ ነው።

የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ እና አለም አቀፍ ትብብር እንዳስታወቀው በዛሬው እለት ታህሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም በጂቡቲ ሊካሄድ የነበረው የሁለቱ መሪዎች ስብሰባ በቴክኒክ ጉዳዮች ምክንያት ተራዝሟል። የተኩስ ማቆምን ጨምሮ የእርዳታ አቅርቦትን ማሳለጥ በሚቻልበት ሁኔታ በጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኡመር ጊሌ አደራዳሪነት ሊካሄድ የነበረው ድርድር ወደ ቀጣይ የፈረንጆቹ አመት መጀመሪያ ወር (ጥር) መራዘሙ ተጠቁሟል።

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር የዛሬው እለት ታህሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም የጂቡቲው ስብሰባ ሊካሄድ ታስቦ እንደነበር አረጋግጦ የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድርድሩ መራዘሙ እንደተገለጸለት አስታውቋል። በምክንያትነት የተገለጸለትም የፈጥኖ ደራሹ ሀይል ተወካዮች መገኘት ባለመቻላቸው ነው የሚል መሆኑን አመላክቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ አዛዥ ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ወደ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው በፊት በኡጋንዳ ቆይታ ማድረጋቸው ተጠቁሟለ።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button