ፖለቲካትንታኔ
በመታየት ላይ ያለ

ጥልቅ ትንታኔ፡ ስጋት እና ተስፋ ያንዣበበበት የትግራይ ፖለቲካ

በሚሊዮን በየነ  @MillionBeyene

አዲስ አበባ፣ ህዳር 24/2016 ዓ.ም፡- ላለፉት ሶስት አስርት አመታት በመላ ኢትዮጵያ በተለይ በትግራይ ክልል የአንድ ፓርቲ የበላይነት እሳቤ ሲቀነቀን ውሎ አድሯል። በእነዚህ አመታት የመንግሥት እና ፓርቲ ስልጣን መደበላለቅ እንደ አሰራር ቅቡል ሆኖ ኖራል፡፡ “ቅቡልነቱ የሀገሪቱን ህዝቦች ብዙ ዋጋ አስከፍልሏል፤ ልዩነቱ በግልጽ ካልተሰመረ እና ተግባር ላይ ካልዋለ ገና ብዙ ችግር ያስከትላል” የሚሉ ድምጾች መሰማት ከጀመሩ አመታት ተቆጥረዋል። 

ከሰሞኑ ከትግራይ በኩል የሚታዩ ምልክቶች ይህንኑ የሚያመላከቱ ይምስላሉ። ለሁለት አመታት በትግራይ የተካሄደው አውዳሚ ጦረነት በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መቋጨቱን ተከትሎ በስምምነቱ መሰረት የተቋቋመው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በሙሉ አቅሜ መስራት አልቻልኩም፣ የታችኛው የክልሉ መንግስት መዋቅር አይታዘዘኝም ሲል ቅሬታውን ሲያቀርብ ተደምጧል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩን 51 በመቶ የስልጣን ወንበር ህወሓት የተቆጣጠረው ቢሆንም በተለመደው የአስተዳደር ሂደት ማለትም የፓርቲው ሊቀመንበር የክልሉ ፕሬዝዳንት ወይንም ከፍተኛ የመንግስት ስልጣን የመያዝ እሳቤ ግን ተግባራዊ አልተደረገም። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት የፓርቲው ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል ወይንም ምክትላቸው ፈትለወርቅ  ገብረ እግዚአብሔር ሳትሆን የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ አባሉ አቶ ጌታቸው ረዳ ሁነዋል። 

ከተለመደው የአስተዳደር አወቃቀር ወጣ ማለቱ የችግሩ መንስኤ መሆኑና በፓርቲው ውስጥ የስልጣን ሽኩቻ እንዲገን አድርጓል የሚሉ አስተያየቶችም ተበራክተዋል። 

በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የአሲምባ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶሪ አስገዶም ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ “በትግራይ አሁናዊ የፖለቲካ ሁኔታ ስጋቱ ይበዛል ወይንስ ተስፋው?” ስንል ለጠየቅናቸው ጥያቄ፣ በህወሓት እና በግዜያዊ አስተዳደሩ መካከል የተፈጠረው ሁኔታ በግዜ ካልተፈታ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ጠቁመው እንደ ፓርቲ ስጋቱ ስላየለብን ልዩነቶቻቸውን በሰለጠነ መንገድ እንዲፈቱ መግለጫ ሁሉ አውጥተናል ብለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“የትግራይ ህዝብ ከፍተኛ ሀዘን ውስጥ በገባበት ሰዓት፣ የስልጣን እሰጥአገባ ውስጥ መገኘታቸው የፈጠረው አሳዛኝ ስሜት ከፍተኛ ነው ያሉት” ሊቀመንበሩ በክልሉ ከሰማዕታቱ መርዶ ጋር ተያይዞ የተተከሉት የሀዘን ዳሶች ሳይፈርሱ እዚህ ውስጥ መግባታቸው አሳዛኝና መሆን ያልነበረበት ጉዳይ ነው ብለዋል። የትግራይ ህዝብም እያለ ያለው በዚህ ሰአት እንደዚህ አይነት ልዩነት መፈጠር አልነበረበትም የሚል ነው ሲሉ አብራርተዋል። በሰላም ካልፈቱት እና አለመግባባቱ ከቀጠለ ግን ስራ መስራት የማይቻልበት ደረጃ ይደረሳል፤ ለክልሉ አደጋ ይሆናል ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ አክለው ገልጸዋል።

የክልሉ ፖለቲካ ምህዳር ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ሊቀመንበሩ ከአምስት አመታት በፊት እንደነበረው ነው የተቀየረ ነገር የለውም ብለዋል። በትግራይ የፖለቲካ ምህዳሩ ባለመስፋቱ በክልሉ በሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና በህወሓት መካከል አለመግባባት መኖሩን ጠቁመው ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሰልፍ ለማድረግ ፈልገው ተከልክለዋል፣ ጭራሽ ሰልፍ ለማድረግ በወጡት ላይም ድብደባ ተፈጽሟል ሲሉ ሁኔታውን በአብነት አስቀምጠዋል።

“ይሄ ሁሉ ጦርነት ተደርጎ፣ ጦርነቱ ላይ ደግሞ ሁላችንም ተሳትፈን፣ የጋራ የሆነ አስተዋጽኦ አድርገን ነበር” ሲሉ ያወሱት ዶሪ አስገዶም በዚህም ሳቢያ የፖለቲካ ምህዳሩ ይሰፋል ብለን በጉጉት ስንጠብቅ ነበር፣ ነገር ግን በህወሓት የቆየ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ሊሳካ አልቻለም ብለዋል።

በክልሉ የምትታተመው ውራይና የተሰኘች መጽሔት ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው አረጋዊን የክልሉ አሁናዊ የፖለቲካ እሰጣገባ እንዴት ተፈጠረ ስንል ላቀረብንለት ጥያቄ በሰጠን ምላሽ፤ አሁን በክልሉ የተፈጠረው ሁኔታ ከነባሩ የአንድ ፓርቲ የበላይነት እና አሰራር ወጣ ባለ መልኩ በትንሹም ቢሆን ሌላ አካላት ስለገቡበት የተፈጠረ ነው ሲል ገልጿል። 

በጊዜያዊ አስተዳደሩ ከህወሓት ስራ አስፈጻሚ አባላት ይልቅ ሌሎች የጦር አመራሮች ከፍተኛ የስልጣን እርከን መያዛቸውን እና 49 በመቶ የሚሆነውን የአስተዳደሩን ስለጣን የያዙት ደግሞ ከፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አመራር ውጭ የሆኑት ሙሁራን እና የተቃዋሚ ፖለቲካ አመራሮች መሆናቸውን አውስቷል።

በክልሉ ያለው የፖለቲካ ውጥረት ወደ ቀውስ ያመራል የሚል እምነት የለኝም ያለን ጋዜጠኛ ጌታቸው በህወሓት ውስጥ የተፈጠረው ነገር የውስጥ የስልጣን ሽኩቻ በመሆኑ በሰላማዊ መንገድ ይፈታል የሚል እምነት አለኝ፣ ቢበዛ ከሃላፊነታቸው የተወሰኑትን በማንሳት ይጠናቀቃል እንጂ ሌላ መልክ አይኖረውም ሲል ገልጿል።

በመቀለ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ስትራቴጂ ጥናት የትምህርት ክፍል መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር እና የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ሁኔታ ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር አሰፋ ለአከ በበኩላቸው “ከድሮም የክልሉ የፖለቲካ ምህዳር ጠባብ ነው፣ አሁንም ከፋ እንጂ ሰፋ የሚባል ነገር የለም” ሲሉ ገልጸው በትግራይ የተዋቀረው ጊዜያዊ አስተዳደር ችግር የገጠመው በዚህ ሳቢያ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት የሚዋቀረው ግዜያዊ አስተዳደር ሁሉን ያቀፈ አንዲሆን ስለሚደነግግ በዚህ መሰረት ብዙዎች የክልሉ ፖለቲካ ይስተካከላል በሚል ተስፋ አድርግው እንደነበር ጠቁመው፣ ነገር ግን በፖለቲካ ምህዳሩ ምክንያት ተፈጻሚ አልሆነም ሲሉ አብራርተዋል።

በክልሉ የፖለቲካ ምህዳር የፓርቲ እና የመንግስት የሚባል ቅርጽ የሌለው ሁለቱን መዋቅር ጠቅልሎ የያዘ አንድ ፓርቲ እንደነበር ያወሱት ረዳት ፕሮፌሰሩ ክልሉን ሲመራ የነበረው እና የዴሞክራሲ ባህል የሌለው ፓርቲ እያስተዳደረው ባለው ክልል የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋ መጠበቅ ሞኝነት ነው ብለዋል።

“ከመጀመሪያው ጀምሮ የግዜያዊ አስተዳደሩ የአወላለፍ ችግር (birth defect) አለው” ሲሉ የጠቆሙት ረዳት ፕሮፌሰሩ “ሲወለድ ጀምሮ ጨንግፏል” ባይ ናቸው። አሁን የተጀመረው የጊዜያዊ አስተዳደሩ አማካሪ ካውንስል መቋቋም ያስፈለገው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ብዚሁ አማካኝነት ነው፣ እሱን ለማስተካከል ተብሎ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የጦርነቱ ሚና በክልሉ ፖለቲካ

አሁን ለሚታየው የክልሉ የፖለቲካ ሁኔታ ጦርነቱ ያሳደረው ተጽእኖ ወይንም ሚና እስከምን ድረስ ነው? ስንል የጠየቅናቸው የአሲምባው ሊቀመንበር ዶሪ አስገዶም ጦርነቱ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አስታውቀው ጦርነቱን ሲመራ የነበረው በዋናነት ህወሓት ይሁን እንጂ ሁሉም ተሳታፊ ነበር ስለዚህ ሁሉንም ሊያሳትፍ የሚችል፣ ትግራይን በቀጣይ ወደተሻለ ሁኔታ ሊያሻግር የሚችል፣ ሁሉም እኩል የሚንቀሳቀስበት የፖለቲካ ሜዳ ሊኖር ይገባል የሚለው እሳቤ በስፋት መንቀሳቀሱ የጦርነቱ ውጤት ነው ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

“ጦርነቱ የወለደው ችግርም አለ፣ ከጦርነቱ በኋላ የተሻለ ነገር ይመጣል፣ የፖለቲካ ምህዳሩ ይሰፋል፣ አቃፊ የሆነ መንግስት ትግራይ ላይ ይመሰረታል፣ ሁሉም ሰው ሀሳቡን ለማስረጽ ሜዳው ክፍት ይሆናል” የሚል ጉጉት በሁሉም ሰዎ ዘንድ መፍጠሩን ጠቁመው ይሄንን ማስተናገድ ህወሓት አቅቶታል ሲሉ አመላክተዋል። “ህዝቡ የመጣውን ጠላት ተባብረን ነው የመከትነው፤ አሁን በሁሉም ጉዳይ እንዲሁ ማድረግ እንፈልጋለን ነው እያለ” ያለው ብለዋል።

ጋዜጠኛ ጌታቸው አረጋዊ የጦርነቱ ዋነኛ ሚና በክልሉ ውሳኔዎች ላይ ከፓርቲው ተወካዮች ውጭ ሌሎች ሚና እንዲኖራቸው በር መክፈቱ መሆኑን ጠቁሟል። ጋዜጠኛ ጌታቸው ሁሉንም ነገር ይወስን የነበረው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ እና ፖሊስ ቢሮ እንደነበር አውስቶ በጦርነቱ ምክንያት ግን በውሳኔዎቹ ላይ ሌሎች በተለይም በትጥቅ ትግሉ አብረዋቸው የነበሩ ነገር ግን ወደ ውትድርናው አዘንብለው የነበሩት እንዲሳተፉ ሁኗል፣ በትግራይ የፖለቲካ ውሳኔ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አስችሏል ብሎናል።

የህወሓት ብቻ ውሳኔን ይሆን የነበረውን አስቀርቷል ያለን ጌታቸው ይሄ ለክልሉ ፖለቲካ ምህዳር መስፋት ተጨማሪ ስንቅ ይሆናል የሚል እምነት እንዳለው አስታውቋል።

ጦርነቱ ገና አልተጠናቀቀም፤ የኤርትራ እና የአማራ ሀይሎች አሉ፣ የተፈናቀሉት አልተመለሱም፣ ስለዚህ በዚህ ሁኔታ ላይ ባለ ክልል ላይ ውሳኔ የሚያሳልፈው ፓርቲው ብቻ ሳይሆን የጸጥታ ሀይሉም ጭምር መሆኑን ጠቁሟል።

ብዙ ሰው ጦርነቱ የትግራይን የፖለቲካ ሁኔታ ይቀይረዋል ብሎ ጠብቆ እንደነበረ የገለጹልን ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ ነገር ግን ጦርነቱን ለመቀልበስ በህዝባዊ ማዕበል የተፈጠረውን የትግራይ መከላከያ ሀይል (ቲዲኤፍ) መቀሌን ሲቆጣጠር እና የፌደራል መንግስቱ ትግራይን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ የተፈጠረውን ህዝባዊ አንድነት ህወሓት በብልጠት ጠልፎ (ሀይጃክ) ወስዶታል፤  ነጻ እና ገለልተኛ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረውን ሀይል በበላይነት በብልጠት ተቆጣጠረው ሲሉ አብራርተዋል።

የፌደራል መንግስቱ ሚና በክልሉ ፖለቲካ

ለአሁናዊው የክልሉ ፖለቲካ የፌደራል መንግስቱ ሚና ይኖረው ይሆን ስንል የጠየቅናቸው የአሲምባው ዶሪ አስገሮምም ሆነ ጋዜጠኛ ጌታቸው አረጋዊ እንዲሁም ረዳት ፕሮፌሰሩ ዶ/ር አሰፋ ሁሉም በተመሳሳይ የመለሱት አለው የሚል ሲሆን ዋነኛው ሚናው የፕሪቶርያውን ስምምነት በተቀመጠለት አቅጣጫ እንዲፈጸም ባለማድረጉ ነው ብለውናል።

ከፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ጋር በተያያዘ የፌደራል መንግስቱ ሊፈጽማቸው የሚገቡትን በሙሉ አልተገበረም ያሉት ዶሪ አስገዶም በተለይም በስምምነቱ መሰረት የፌደራል መንግስቱ የግዜያዊ አስተዳደሩ አካል መሆን እየቻለ አለመሳተፉ እና ሁሉም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲወከሉ ግፊት ማድረግ እየቻለ አለማድረጉ ትልቁ ስህተቱ ነው በለዋለ። ይህም ለክልሉ አሁናዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት ትልቅ ሚና አለው ሲሉም ገልጸዋል። ነገር ግን በህወሓት ላይ ለሚታየው የፖለቲካ ሽኩቻ ተጠያቂ መሆን ያለበት እራሱ ህወሓት ነው ብለዋል። የፌደራል መንግስቱ ቀጥታዊ ያልሆነ በተዘዋዋሪ ግን አስተዋጽኦ ሊኖረው እንሚችልም ጠቁመዋል።

ጋዜጠኛ ጌታቸው አረጋዊ በበኩሉ በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት በተለይ የክልሉ ግዛታዊ አንድነት አለመከበሩ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው አለመመለሳቸው የፌደራል መንግስቱ ችግር ነው ሲሉ ገልጸው ይህ ለክልሉ ፖለቲካ አለመረጋጋት ሚናው ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል። ይህም በክልሉ አሁናዊ ፖለቲካ በመቅረብ ላይ የሚገኝ አንዱ አጀንዳ መሆኑን ጠቁመው የግዜያዊ አስተዳደሩ ይህንን አልፈጸመም ተብሎ የሚተች ቡድን ተፈጥሯል ብለዋል።  

የክልሉ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ቁመና

የትግራይ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አሁኑ በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ፣ የክልሉ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ጠርጎ ይወስዳቸው ይሆን ወይንስ ክልሉን ከአውራ ፖለቲካ ቀንበር ይገላግሉት ይሆን ስንል የጠየቅናቸው የአሲምባ ፓርቲ ሊቀመንበሩ ዶሪ አስገዶም አብዘሃኛው የክልሉ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተመሰረቱበት ወቅት በጣም አስቸጋሪ በነበረበት ወቅት እንደነበር አስታውሰው ከአረና ውጭ ያሉት በተመሰረቱ በተወሰነ ግዜ ውስጥ ነው ክልሉ ወደ ጦርነት ማምራቱን አስታውቀዋል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከህወሓት የሚደርስባቸውን ጫና ተቋቁሞ ህልውናቸውን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ትንቅንቅ ማድረጋቸውን እና “አሁን ላይ ህልውናቸው መጠበቁን ጠቅሰው ህወሓት በኢኮኖሚ የፈረጠመ ነው፣ ስልጣን በእጁ ነው፣ ጠመንጃውም የእሱ ነው፣ ከወረዳ በታች ባሉ ጣቢያዎች ጭምር የተዘረጋ ኔትዎርክ አለው፣ ይህንን ኔትወርክ ለመስበር ግዜ ያስፈልጋል፣ ይህንን ሁሉ ተቋቁመው መቆየታቸው እራሱ ትልቅ አቅም ነው” ብለውናል። በግዜያዊ አስተዳደሩ ላይ ተቃዋሚዎቹ እንዳይሳተፉ ከፍተኛ ሴራ ነው ህወሓት የሰራው ሲሉ ገልጸው ነገሮች እንዲስተካከሉ ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው፤ ነገር ግን ግዜ የሚወስድ በመሆኑ ግዜ ያስፈልገናል ብለዋል።

“ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይጠናከሩ እና አማራጭ ሆነው እንዳይወጡ ሌት ተቀን እየሰራ ያዳከማቸው ህወሓት እራሱ ነው” ሲሉ የገለጹት ሊቀመንበሩ ህዝቡን እንዳናገኝ፣ አባላት እንዳናፈራ ያደረገን ህወሓት ነው፣ ከዚህ አፈና ለመውጣት ተቃዋሚዎች የሰራነው ስራ አለ ብለዋል።

በክልሉ በስፋት የሚነገረው ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አቅም እንደሌላቸው ተደርጎ መሆኑን የገለጹልን የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህሩ ዶ/ር አሰፋ ለአከ ይሄ ፕሮፓጋንዳ ነው፣ በተለይ አውራው ፓርቲ የህወሓት እየፈጠረው ያለው ምስል ነው ሲሉ ተችተዋል። ህወሓትን ከመንቀፍ የዘለለ ራዕይ እና ፖሊሲ የላቸውም በሚል ቅቡልነት እንዳያገኙ የሚሰራ ስራ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።

መታወቅ ያለበት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ህወሓትን ለማወደስ የተቋቋሙ አለመሆናቸው ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ የጠራ የፖለቲካ መስመር ያላቸው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ሁሉ ደካሞችም መኖራቸው መርሳት የለብንም ብለዋል።

“ህወሓት ልምድ ያለው ፓርቲ ነው ግን ክልሉን የት አደረሰው ብለን ከፈተሽን እነዚህ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችስ ስልጣን ቢይዙ ከዚህ የከፋ ምን ሊያመጡብን ይችላሉ” ሲሉ የጠየቁት ረዳት ፕሮፌሰሩ “ቢከፋ ቢከፋ እንደ ህወሓት መሆን አያቅጣቸውም” ሲሉ ገልጸዋል። ለአንድ ፓርቲ ተብሎ የተመሰረተ አገር የለም በማለት፣ በአመክንዮ ማየቱ የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጠንካራ ባይሆኑስ ምን ይደንቃል፣ እንዲዳከሙ ብቻ ሳይሆን እንዲጠፉ ጭምር ነው ህወሓት ሲሰራ የነበረው ሲሉ የተቹት ዶ/ር አሰፋ ይህንን ሁሉ ጫና ተቋቁመው መቆየታቸው እራሱ ጠንካራ ለመሆናቸው ማሳያ ነው፣ በመቀሌ በዋና ከተማዋ ይሻላቸዋል እንጂ በሌሎቹ የክልሉ ከተሞችማ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ የሚያስችላቸው ነገር የለም ሲሉ ገልጸዋል።

የክልሉ ባለሃብቶች እኮ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን መደገፍ አይችሉም፤ የሚከተልባቸውን ያውቁታል ሲሉ ስጋታቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ያጋሩት ረዳት ፕሮፌሰሩ ይህንን ሁሉ መቋቋም የቻሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዴት ነው ክልሉን መምራት አይችሉም የሚባለው ብለዋል።

ጋዜጠኛ ጌታቸው አረጋዊ በበኩሉ የክልሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቁመና ገና ክልሉ በሚፈልገው ደረጃ የተጠናከሩ አይደሉም ሲሉ ገልጾ ገና እስከታች የሚወርድ አደረጃጀት አለመፍጠራቸውን፣ በአንድ ላይ ሰብሰብ ብለው አለመደራጀታቸውን በአብነት ጠቅሷል። የፖለቲካ ሜዳውን በብቸኝነት ህወሓት ሲዘልበት ስለነበረ በብቸኝነት እስከታች ድረስ መዋቅሩን የዘረጋው ህወሓት ነው ሲሉ ገልጸዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button