ፖለቲካዜና ትንታኔ
በመታየት ላይ ያለ

ጥልቅ ትንታኔ፡ የህዳሴ ግድብ ድርድሮች እና ቀጣይ ውጤቶች

በሚሊዮን በየነ @MillionBeyene እና አብዲ ቢየንሳ @ABiyenssa

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10/2016 ዓ.ም፡- ኢትዮጰያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ከጀመረች ድፍን 12 አመታትን አስቆጥራለች፡፡ ይህ ታላቅ ተስፋ የተጣለበት የህዳሴ ግድብ ጳጉሜን 5፣ 2015 ዓ.ም. አራተኛው እና የመጨረሻው የውሃ ሙሌት የመጠናቀቁ ብስራት ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በስተላለፉት መልዕክት “ብዙ ፈተና ነበረው፤ ወደኋላ እንድንመለስ ብዙ ተጎትተን ነበር። በውስጥ ፈተና በውጭ ጫና ነበረብን። ከፈጣሪ ጋር የመጣውን ሁሉ ተቋቁመን ለዚህ ደርሰናል።” ብለዋል።

ለኢትዮጵያውን ደስታን የፈጠረው ይህ ተግባር ግብፅን ማስቆጣቱን የማይጠበቅ አይደለም፡፡ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህ የውሃ ሙሌት የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ጥቅምና መብት እንዲሁም የውሃ ደኅንነታቸውን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ አለመሆኑን በመግለፅ ተቃውመዋል፡፡” ድርጊቱ በዓለም አቀፍ ሕግ መርሆዎች የጣሰ ነው ሲሉም ሚኒስትሩ ተልፀዋል፡፡

ሱዳንን ጨምሮ ሁለቱ ሀገራት መካከል ለበርካታ ጊዚያት በአባይ ዉሃ አጠቃቀም ላይ በተደጋጋሚ ውይይት ተደርጓል፡፡ ከቅኝ ግዛት ውሎች ይከበሩ እስከ እኔ የፈልኳቸው አደራዳሪዎች ያደራድሩን የሚሉ ሀሳቦች በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከግብጽ በኩል ሲነሱ የነበሩ ሀሳቦች ነበሩ። ኢትዮጵያ ደግሞ ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ብቻ ይሁን የሚል አቋም ስታራምድ ነበር።

በግድቡ ዙሪያ ተደጋጋሚ በሶስቱ ሀገራት ድርድር ቢካሄድም ምንም ነገር ጠብ ሳይለ ያለስምምነት ተበትኗል። ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በአሜሪካ አደራዳሪነት የተካሄደው እንዲሁ እሱም ያለስምምነት ከመበተኑ ባለፈ በቀጣይ ኢትዮጵያ ከሶስትዮሽ ውጭ ያሉ ድርድሮች በአፍሪካ ህብረት ብቻ መሆን እንዳለበት ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ ነው ተብሎ በብዙዎች ዘንድ ተገልጿል። በቅርቡ ደግሞ በተመሳሳይ ከአፍሪካ ህብረት አዳራዳሪነት ውጭ በተባበሩት አረብ ኤሜሬት አደራዳሪነት ሶስቱ ሀገራት በመነጋገር ላይ ይገኛሉ።

የድርድሩን ሂደት የማቀላጠፍ ሚና በመጫወት ላይ ያለችው የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሸክ ሻህቡት ናህያን አል ናህያን ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር በነበራቸው ቆይታ ድርድሩ በቅርቡ በስምምነት ይቋጫል ብለው ተናግረዋል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ በግብጽ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ጋር ከተወያዩ በኋላ የድርድሩን ሂደት በአራት ወራት ውስጥ ለመቋጨት መስማማታቸው መገለጹን ተከትሎ የመጀመሪያው ዙር ውይይት በካይሮ ተካሂዷል:: ይህን ተከትሎ የካይሮው ውይይት ያልተሳካው በኢትዮጵያ ያልተቀየረ አቋም ምክንያት ነው ሲሉ የግብጽ የመስኖ ሚኒስትሩ ሃኒ ሳዊላም ተናግረዋል።

ቀጣዩ የሶስቱ ሀገራት ውይይት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገልጿል፤ ምን ይጠበቃል ስንል ሙሁራንን ጠይቀናል።

የሃይድሮ ፖለቲክስ ተመራማሪ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት የትምህርት ክፍል የሶስተኛ ዲግሪ እጩ ጋሻው አይፈራም በእኔ አረዳድ በቀጣይ የሚካሄዱ ድርድሮች ውጤት የሚያመጡ አይሆኑም ሲሉ አስተያየታቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። የናይል ፖለቲካ ተፈጥሮው ውጤት ለማምጣት የሚያስችል አይደለም፤ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ግትርነት ምንም አይነት አዲስ ውጤት እንዳያመጣ ያደርገዋል ያሉት ጋሻው አይፈራም፣ የግብጽ የናይል ፖለቲካ ውሃው ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም፤ የመንግስታቱ የህልውና ማስጠበቂያ፣ መለያ እና ቅቡልነት ማግኛ ተደርጎ ነው የሚቆጠረው፤ በተጨማሪም የቀጠናዊ ፖለቲካዋ መቃኚያም ነው፤ ይህም በመሆኑ ለድርድር የሚያመች ነገር የለውም ብለዋል።

የደቡብ ፍሎሪዳ ዩኒቨርስቲ መምህሩ እና የውሃ ባለሞያው ዶ/ር ጥሩሰው አሰፋ በበኩላቸው በግብጽ በኩል የተለየ ነገር ካልመጣ በስተቀር በቀጣይ ድርድሮች ይህ ነው የሚባል ለውጥ ይመጣል ብለው እንደማይጠብቁ ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል። የግብጽ የውሃ እና መስኖ ሚኒስትር ከካይሮው ድርድር በኋላ በሰጡት መግለጫ የሶስትዮሽ ድርድሩ ያለውጤት መጠናቀቁን እና ያለውጤት ለመጠናቀቁ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያ አሁንም አቋሟ ባለመቀየሩ ነው ማለቱን ያስታወሱት ዶ/ር ጥሩሰው በቀጣይ ድርድሮች እዚህ ግባ የሚባል ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ብለው እንደማይጠብቁ ጠቁመዋል።

የታሪክ ሙሁሩ እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አቶ ጸጋዘአብ ካሳ በበኩላቸው በህዳሴ ግድበ ዙሪያ የኢትዮጵያ መንግስት ብዙ ነገሮች በፖለቲካዊ ውሳኔዎቹ አበላሽቶ ነው ወደ ድርድር የገባው ሲሉ ገልጸው እነዚህ ነገሮች ሳይስተካከሉ ወደ ድርድር መግባት የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ይሳጣል ሲሉ ስጋታቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ አጋርተዋል። ከአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ወጥቶ በተባበሩት አረብ ኤሚሬት አደራዳሪነት መካሄዱን ከመንግስት ስህተቶች መካከል አንዱ ነው ሲሉ በአብነት ያስቀመጡት አቶ ጸጋዘአብ የህዳሴ ግድብ የአረቡ አለም ሀገራት ጂኦፖለቲካዊ ጥቅም ማስተግበሪያ እየዋለ ነው ሲሉ ተችተዋል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ስለ ቀጣይ ድርደሮች ማውራት ተገቢ አይደለም በማለት ገልጸዋል።

ዶ/ር ስለሺ በቀለ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር እና በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በመካሄድ ላይ ባለው ድርድር ኢትዮጵያን የወከለው ተደራዳሪ ቡድን መሪ ናቸው፤ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለድርድሩ ሂደት ማብራሪያ ሰጥተዋል። ዶ/ር ስለሺ በአዲስ መልክ ድርድሩ የተጀመረው ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ በግብጽ ከግብጹ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ጋር ከተወያዩ በኋላ የድርድሩን ሂደት በአራት ወራት ውስጥ ለመቋጨት ለተደራዳሪዎች መመሪያ መስጠታቸውን ተከትሎ መሆኑን ጠቁመው በመጀመሪያው ድርድር ወቅት አቀራረባችን ካቆምንበት ቦታ ለመጀመር የሚያስችል የውይይት አቀራረብ ነበር፣ የእኛ አቀራረብ በጥሩ መንፈስ ነበር ብለዋል።

በሁለቱ የድርድሩ ቀናት ያደረግነው በድርድሩ ከሚገኙ 16 አንቀጾች በዘጠኙ ላይ አዳዲስ ሀሳቦችንም ጨምረን ያንኑ ኤዲት አድርገን ውይይት አድርገናል ያሉት ዶ/ር ስለሺ በዘጠኙ አንቀጾች ስምምነት ላይ አለመደረሱን አስታውቀው በድርድሩ ወቅት የእኛን ጨምሮ የሶስቱን ሀገራት ሀሳብ አካተን ነው የተለያየነው ብለዋል። በተጨማሪም ዶ/ር ስለሺ መስከረም ወር ላይ ሁለተኛው ምዕራፍ ድርድር አዲስ አበባ እንደሚካሄድ ጠቁመው ቀሪዎቹ 7 የሚሆኑት አንቀጾች ላይ ውይይት ተደርጎባቸው ኤዲት ተደርገው ለሁላችን አመች በሚሆን መልኩ እንዲቀረጽ እንሰራበታለን ሲሉ አብራርተዋል።

አሳሪ ህግ

በኢትዮጵያ በኩል ባለፉት የድርድር ግዜያት ሲቀርብ የነበረው ዋነኛ ነጥብ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በህዳሴው ግድብ ላይ የሚያራምዱት አቋም ለድርድሮቹ ውጤታማነት እንቅፋት ሆኗል የሚል ነበር፤ ይህም በውሀው ሙሌትና በድርቅ ጊዜ ኢትዮጵያ ከግድቡ እንድትለቅ የሚጠይቁት የውሀ መጠን መርህን ያልተከተለና የማይሰራ ነው የሚል ነው።

ግብፅና ሱዳን በዋናነት የሚፈልጉት በድርቅ ጊዜ ካጠራቀማችሁት ውሀ ምን ያክል ትሰጡናለችሁ ይህንንም በአሳሪ ስምምነት አረጋግጡልን የሚለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህን ጉዳይ እንደማትቀበለው በተደጋጋሚ ገልጻለች። ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ያቀረቡት አሳሪ ስምምነት ውስጥ ፈፅሞ መግባት የለባትም ሲሉ በርካታ የሀገሪቱ ሙሁራን ሲገልጹ ቆይተዋል።

ኢትዮጵያ እስከ አሁኑ ድረስ ይህንን አቋሟን ማለሳለሷን የሚያሳይ፣ ግብጽ ደግሞ ይህን ጥያቄዋን ማቆሟን የሚያመላክት ነገር አልታየም። በቀጣይ የድርድር ግዜያት ኢትዮጵያ ይህንን አቋሟን ታለሳልስ ይሆን ስንል የጠየቅናቸው ዶ/ር ጥሩሰው በቀደሙት ግዜያት ባቀረበችው የመደራደሪያ ሀሳቦች የግብጽን ፍላጎት ግምት ውስጥ አስገብታለች ሲሉ ገልጸው ምንም አይነት ማለሳለሻ አያስፈልጋትም ብለዋል።

የግብጾቹ ስጋት በድርቅ ወቅት ውሃ እንዴት ይለቀቅልናል በሚል መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ጥሩሰው ከዚህም ጋር ተያይዞ ድርቅ ሲሆን ኢትዮጵያ ምንም አይነት ውሃ ሳትጠቀም ትልቀቅ የሚል አቋም ስታንጸባርቅ ቆይታለች ይህም የማይሆን ነው ሲሉ አስታውቀዋል። ግብጽ በዚህ ሁሉ ጉዳዮች ኢትዮጵያ እንድትፈርም የምትፈልገው ከአባይ ውሃ ምንም አይነት ተጠቃሚነት እንዳይኖራት ለማድረግ ነው ሲሉ የገለጹት ዶ/ር ጥሩሰው ለመስኖም ይሁን ለመጠጥ ወንዙን አንጠቀምም ብለን እንድንፈርም ነው ፍላጎቷ ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ይህም ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ብለዋል። ግብጾቹ ከመጀመሪያው ጀምሮ የቅኝ ግዛት ውሎች ይከበሩ ማለታቸው ሙሉ በሙሉ እኛ ብቻ እንጠቀም ለማለታቸው ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዶ/ር ስለሺ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ ከታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ተደራዳሪዎች ኢትዮጵያ በቀጣይ በወንዙ እንዳታለማ የሚያስር አይነት ስምምነት እንዲወጣ ይፈልጋሉ ሲሉ ገልጸው ይህ ጥንቃቄ የሚያስፈልግ አገራዊ ፍላጎት ነው፣ ይህም እንዳይጣስ በጥንቃቄ የምናየው ጉዳይ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

ዶ/ር ስለሺ አሳሪ ህግ አንፈርምም ሲሉ አልተደመጡም፣ እንዲያውም አሳሪ ህጎቹ ላይ ትኩረት የምንሰጠው አንቀጾቹ የኢትዮጵያን የመልማት መብት የማይገድቡ፣ ነገር ግን የታችኞቹ ሀገራት ላይ ደግሞ ጉልህ ጉዳት የሚያስከትል ነገር ላይ የኢትዮጵያ ውሃ አጠቃቀም እንዳይሄድ ነው፤ ሲሉ ጉዳዩ አንፈርምም ሳይሆን ምንምን ተካቶበት ወይንም ምንምን ሳይካተትበት በሚለው መሆኑን ጠቁመዋል።

በድርድሩ ሂደት ዋነኛው የሚያጨቃጭቀን ነገር ድርቅ ቢከሰት ያን ድርቅ እንዴት አድርገን እንቋቋመዋለን የሚለው መሆኑን ያብራሩት ዶ/ር ስለሺ ይህም ሀሳብ ቁጥሮች ስለሚይዝ፣ ቁጥሮች ደግሞ የውሃ ክፍፍል ጉዳይ እንዳይሆኑ ነው ጥንቃቄ እየወሰድን ያለነው ሲሉ ተደምጠዋል። ከህዳሴ ግድብ በላይ የሚሰሩ የወደፊት ፕሮጀክቶቻችን በስምምነቱ እንዳይደናቀፉ ፎርክሎዠር እንዳያመጡ ጥንቃቄ የምናደርግበት ነው ብለዋል።

የሀይድሮ ዲፕሎማሲ ተመራማሪው ጊቶሬ ኢሳያስ ኢትዮጵያ አቋሟን ታለሳልስ ይሆን ተብለው ከአዲስ ስታንዳርድ ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ ኢትዮጵያ በጉዳዮቹ ዙሪያ ስምምነት ለማድረግ የሚያስችላት ሁኔታ ቀላል አለመሆኑን ጠቁመው በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በህዝቡ ዘንድ የተቀረጸ ትልቅ ምስል አለ፤ መንግስት ትንሽ ሸርተት ካለ የሚጠብቀው ተቃውሞ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም መንግስትን የሚቃወሙ ሀይሎች ትልቅ መጫወቻ አገኙ ማለት ነው ያሉት ጊቶሬ ኢሳያስ ሌላው ቢቀር በገዢው ፓርቲ ውስጥም ምቾት የማይሰጥ ሁኔታን ይፈጥራል፣ በአማራ እና ኦሮሞ ብልጽግና ውስጥ ያለውን እሰጥ አገባ የሚያቀጣጥለው ይሆናል፣ እንደ ሀገርም ክህደት ተደርጎ ሊቀርብ ይችላል ሲሉ ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

በቀደመው የቅኝ ግዛት ውል ከፍተኛ ተጠቃሚዎቹ ግብጽ እና ሱዳን ናቸው፣ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ምንም አይነት ድርሻ የላቸውም ያሉት ተመራማሪው ውሉ መሰረት ተደርጎ የውሃ ድርሻቸው እንዲጠበቅላቸው የሚያስቡ ከሆነ የሚቻል አይሆንም፤ የላይኛዎቹ ተፋሰስ ሀገራት ለወንዙ ውሃ ከፍተኛ አበርክቶ ስላላቸው መልማትን ይፈልጋሉ በመሆኑም የድርሻ ጉዳይ ተቀባይነት አያገኝም ሲሉ ገለጸዋል።

የሱዳን ጉዳይ

ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ባደረገቻቸው የሶስትዮሽ ድርድሮች እሰከ ቅርብ ግዜያት ድረስ ከሱዳን በኩል ይህ ነው የሚባል የከረረ ተቃውሞ ቀርቦባት አያውቅም። እንዲያውም የኢትዮጵያን አቋም በተለያየ ግዜ ደግፋለች በሚል በግብጽ መገናኛ ብዙሃን እና በምሁሯኖቿ ተብጠልጥላለች።

ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በሱዳን የተፈጠረው የእርስ በርስ ግጭት የሀይል አሰላለፍ ለውጥ የሚፈጥር ይመስላል የሚል ትንታኔ ብቅ ማለት ጀምሯል፡፡ በአብዱል ፈታህ አልቡርሃን የሚመራው የሀገሪቱ የጦር ሀይል ከግብጽ በኩል ግለጽ የሆነ ድጋፍ እየተሰጠው መሆኑ ደግሞ ሱዳን በግብጽ የተጽዕኖ እጅ ሙሉ በሙሉ ገብታለች የሚል አንድምታን ፈጥሯል።

ከዚህ በኋላ በሚኖሩ የሶስትዮሽ ድርድሮች ሱዳን ወደ ግብጽ ማድላቷ፤ ሁኔታውም ለግብጽ የተመቻቸ አይሆንም ወይ ስንል የጠየቅናቸው የሀይድሮ ዲፕሎማሲ ተመራማሪው ጊቶሬ ኢሳያስ አሁን በተፈጠረው ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ቀድሞም ቢሆን በሱዳን ፖለቲካ ትልቁ ተዋናኝ ሚሊተሪው ነው፤ በሱዳን ፖለቲካ ውስጥ የግብጽ እጅ ሰፊ ነው ሲሉ ገልጸው ዛሬ ሳይሆን ቀድሞም ግብጾች በሱዳን ፖለቲካ ላይ ዋነኛ ተዋናይ ናቸው ብለዋል።

በርካታ ተዋጊዎችን እያሳተፈ በመሆኑ አሁን ባለው ሁኔታ የእርስ በርስ ግጭቱ ሚዛን ወደየት እንደሚያጋድል ለመተንበይ አዳጋች የሚያደርገው የሱዳን አጎራባች ሀገራት እና ሀያላን ሀገራት በመሳተፍ ላይ በመሆናቸው ነው ሲሉ የገለጹት ጊቶሬ ኢሳያስ ከምንም በላይ ግን የሱዳን ተፋላሚ ሀይሎች ውጤት በይበልጥ በግብጽ እና ኢትዮጵያ የሚወሰን ይመስላል ብለዋል። ኢትዮጵያ ሁኔታውን በይበልጥ በመከታተል ቀመሯን ማስተካከል ይገባታል ሲሉ ምክራቸውን ሰንዝረው ካልሆነ ግን ግብጽ በሱዳን ያላትን የበለጠ ተጽእኖ በመጠቀም የበላይነት ልትጎናጸፍ ትችላለች፣ ይህም የሱዳንን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በመቅረጽ በኩል ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ በተለይ ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የሚኖራት አቋም በዚሁ መቃኘቱ የማይቀር ይሆናል ሲሉ ስጋታቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ አጋርተዋል።

እንደገና በተጀመረው እና በካይሮ በተካሄደው ድርድር ሁሉም የሱዳን ተዳራዳሪ ቡድን አባላት መሳተፋቸውን ያስታወቁት ዶ/ር ስለሺ፣ ያሉበት ሁኔታ አስቸጋሪ እንደሆነ ይታወቃል ነገር ግን በካይሮ በነበረው ውይይት ሱዳኖቹ ችግሮቻቸውን ተቋቁመው ለድርድሩ ትኩረት በመስጠት መሳተፋቸውን ገልጸዋል። ሚኒስትሮቹም ተደራዳሪዎቹም ነበሩ ያሉት ዶ/ር ስለሺ ለቴክኒካል እና ሌጋል ተብሎ የተተወ የለም ሁሉንም አንድ ላይ አይተናል፣ ተወያይተናል ብለዋል።

የሃይድሮ ፖለቲክስ ተመራማሪ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት የትምህርት ክፍል የሶስተኛ ዲግሪ እጩ ጋሻው አይፈራም በበኩላቸው ሱዳን በግድቡ ዙሪያ ይህ ነው የሚባል አቋሟን በአደባባይ አሰምታ አታውቅም ሲሉ ገልጸው የቀጠናውን ወቅታዊ ሁኔታ እየተመለከተች ነበር የድጋፍ ቀመሯን ትሰራ የነበረው፣ በየድርድሮቹ አንድ ግዜ ለኢትዮጵያ አንድ ግዜ ለግብጽ ድጋፍ በመስጠት ዥዋዥዎ ስትጫወት ነበር ሲሉ አውስተዋል። የአልቡርሃን ቡድን አሁን ባለው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት አሸናፊ ሁኖ ከወጣ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ በግብጽ ተጽእኖ ስር መውደቁ የማይቀር ነው፣ በድርድሮቹ ግብጽ ጉልበት ታገኛለች ሲሉ አብራርተዋል።

በሌላ መልኩ የሀይድሮ ዲፕሎማሲ ተመራማሪው ጊቶሬ ኢሳያስ በቀደሙት ግዜያት ኢትዮጵያ በአለም መድረክ ተቀባይነቷ በጥሩ ደረጃ ላይ እነደነበር አስታውሰው በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ ምስል እያሽቆለቆለ ይገኛል፣ በተለይ ደግሞ በትግራይ የተካሄደው የእርስ በርስ ግጭት፣ በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚታየው ሰላም ማጣት በምዕራቡ አለም እንድትትው እንዳደረጋት ጠቁመው በድርድሩ ሂደት ከሱዳን በተጨማሪ አለም አቀፍ ሁኔታዎች ለግብጽ ጉልበት ይሆኗታል ሲሉ ስጋታቸውንለአዲስ ስታንዳርድ አጋርተዋል።

ከምዕራቡ አለም ጋር ያለንን ግንኙነት ማሻሻል ይጠበቅብናል ያሉት ጊቶሬ በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ የድርድር አቅም በፖለቲካም በዲፕሎማሲም ወርዷል፣ ፖለቲካዊም ይሁን ኢኮኖሚያዊ ችግር ላይ መሆናቸን ጉልበት አሳጥቶናል፣ ይህም ምዕራቡ አለም በሚያሳድርብን ተጽእኖ የግድቡን ሂደት ማጓተታችን አይቀሬ ያደርገዋል ብለዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button