ፖለቲካዜና ትንታኔ
በመታየት ላይ ያለ

ጥልቅ ትንታኔ፡ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ከአንድ አመት በኋላ ምን አሳካ? ምንስ አላሳካም?

በሚሊዮን በየነ @MillionBeyene

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22/2016 .ም፡ ከአንድ አመት በፊት በደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶርያ ከተማ ለሁለት አመታት ሲካሄድ የቆየው እና አንድ ሚሊየን የሚጠጋ ህዝብ ያስጨረሰው የትግራዩ ጦርነት መቋጫ አገኘ፤ ከተፋላሚዎቹ መካከል የሆኑት የፌደራል መንግስቱ እና የትግራይ ሀይሎች የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ። ልክ የዛሬ አመት የፕሪቶርያው ስምምነት በበርካቶች ዘንድ ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበት በየአቅጣጫው ጭብጨባ እና ሙገሳ ጎረፈለታል፤ እርግጥነው የጭብጨባውን ያክል ባይሆንም ስጋቶችም በወቅቱ ተስተጋብተዋል።

አሁን ላይ የፕሪቶርያው ስምምነት አንድ አመት ሞልቶታል፤ እናም በትግራይ የሚገኙ የክልሉ ሙሁራንን በስምምነቱ ምን ተስፋ ሰንቃችሁ ነበር ስንል ጠይቀን? ተሳካ የሚሉትን እና አልተሳካም የሚሉትን እንዲነግሩን ጋበዝናቸው።

ከትግራይ በኩል ከስምምነቱ ተጠብቁ የነበረው በጣም ግልጽ ነበር የሚል እምነት አለኝ ሲሉ የነገሩን የታሪክ ተመራማሪው እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አቶ ጸጋዘአብ ካሳ ይጠየቁ የነበሩት ዋና ዋና ጥያቄዎች እና እንዲከበሩ የምንሻቸው ህጎች በሰላማዊ መንገድ ምላሽ ያገኛሉ የሚል ተጠባቂ አካሄድ ነበር ብለውናል። ምን ነበሩ ተጠባቂዎቹ ስንል ለጠየቅናቸው ጥያቄም ሲያብራሩ ከሁሉም በላይ ተጠባቂ የነበረው የምግብ እርዳታ እና የመድሃኒት አቅርቦት ያለምንም ገደብ ወደ ለህዝቡ እንዲዳረስ ያደርጋል የሚለው ነው፤ በተጨማሪ ግን ተኩስ ከቆመ እና በሰላማዊ መንገድ ነገሮች ሲፈቱ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንደሚመለሱ የክልሉ የግዛት አንድነት እንደሚጠበቅ ትልቅ ተስፋ ተጥሎባቸው ከነበሩ ጉዳዮች መሃከል መሆናቸውን ጠቁመውናል።

የባይቶና ትግራይ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ዶ/ር ጸጋዘአብ ካህሱ በበኩላቸው ስምምነቱ ወደ ሙሉ ሰላም፣ ልማት ያሸጋግረናል የሚል ተስፋ ነበረኝ ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸው በጠበኩት እና ተስፋ ባደረኩት መጠን ባይሆንም ተማሪዎች እጅግ ውስን በሆነ መልኩ ትምህርት መጀመራቸው፣ ባልተሟላ መልኩም ቢሆን የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠታቸውን ጠቅሰዋል።

ከአመት በፊት የሰላም ስምምነቱ በመፈረሙ ምን ጠብቀው ነበር፣ ይፈጸማል፣ ይሆናል ብለው ምን ተስፋ አድርገው ነበር ስንል ለጠየቅናቸው ጥያቄ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና ስትራቴጂ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህሩ ገ/መድህን ገ/ሚካኤል ለአዲስ ስታንዳርድ ሲመልሱ ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅትከአንድ አመት በኋላ ብዙ ነገሮች እንደሚሻሻሉ ጠብቀው እንደነበር አስታውሰው ለምሳሌ ሁሉም ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው፣ በውሉ መሰረት የኤርትራ ወታደሮች እና የአማራ ሀይሎች ከትግራይ መሬቶች ለቀው ይወጣሉ የሚል ተስፋ እንደነበራቸው ነግረውናል።

በተጨማሪም በአንድ አመት ውስጥ ተቋርጠው የነበሩ የልማት ፕሮጀክቶች ይቀጥላሉ፣ አስተማማኝ መረጋጋት እና ሰላም ተፈጥሮ እናያለን የሚል ተስፋ ነበረኝ ሲሉ ገልጸው በስምምነቱ መሰረት የስምምነቱ አንድ አካል የሆነውን ትጥቅ ማስፈታት፣ ተዋጊዎችን መበተን እና መልሶ ማቋቋም ሂደት (DDR) ጋር በተያያዘ መልሶ ማቋቋሙ ረጂም ግዜ ቢወስድም ቢያንስ ትጥቅ ማስፈታት እና ተዋጊዎችን መበተን ብዙ ርቀት ይሄዳል የሚል እምነት እንደነበራቸው አጋርተውናል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ስምምነቱ ታዲያ ምን ጠቀመ? ምንስ አሳካ?

የፖለቲካ ምሁሩ እና የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ጸጋዘአብ ካሳም ሆኑ የመቀሌ ዩኒቨርስቲው መምህር ገ/መድህን ገ/ሚካኤል ሁሉም ለአዲስ ስታንዳርድር የገለጹት የስምምነቱ ስኬት የተኩስ ድምጽ መቆሙን ነው። በተጨማሪም በሁለቱም በኩል በውጊያ ምክንያት የሚሞተው ቀርቷል፣ ስምምነቱ ያሳካው ይሄን ብቻ ነው ብለውናል።

በትግራይም ሆነ በፌደራልመንግስቱ በኩል ሁሉንም ነገር በጦርነት በማሸነፍ እንፈታዋለን ከሚለው አቋም እና የሀገሪቱ የቆየ ልሙድ ባህል በተለየ መልኩ በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ልዩነቶችን በውይይት አሸናፊ የመሆን መንገድን ለመከተል መወሰናቸው በስኬት ሊታይ ይችላል።

አቶ ጸጋዘአበ በተጨማሪ ስምምነቱ በአንድ አመቱ ከወሰድንለት የተገደበ የትራንስፖርት እና መሰል አገልግሎቶች ናቸው፣ በትንሽም ቢሆን በአየር ትራንስፖርቱ መውጣት መግባት መቻሉ የስምምነቱ ስኬት ነው ብለውናል።

መምህር ገ/መድህን በበኩላቸው ሌላኛው የስምምነቱ ስኬት በክልሉ ሰማይ ላይ የአውሮፕላን እና የድሮን ማንዣበብ መቅረቱ መሆኑን ነግረውናል። በተጨማሪም በአመቱ ይተገበራ ተብሎ ተጠብቆ ከነበረው ትጥቅ ማስፈታት፣ ተዋጊዎችን መበተን እና መልሶ ማቋቋም ሂደት (DDR) ትግበራው ውስጥ የትግራይ ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት በስኬትነት ሊመዘገብ ይችላል ብለዋል።

360 ዲግሪ ተዘግቶ የነበረው ክልል የተወሰነ ዲግሪው መዘጋቱ ቀርቷል፣ የአንድ አመት በጀት መለቀቁ ስምምነቱ ያሳካው ነው ማለት ይቻላል ሲሉም አክለዋል።

በስምምነቱ ያልተሳኩት የትኞቹ ናቸው

የታሪክ ሙሁሩ እና የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ፀጋዘአብ ካሳ ስምምነቱ ያላሳካው ትልቁና ተጠባቂ ጉዳይ እርዳታ እና መድሃኒት ያለምንም ገደብ ወደ ህዝቡ እንዲዳረስ ያደርጋል የሚለው መሆኑን ገልጸው ይህ ግን አልሆነም፣ አልተሳካም፤ ከስምምነቱ በኋላ ይባስ ብሎ በአሳፋሪ ሁኔታ ሁሉም ቆመ ብለዋል። የመቀለ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ገብረመድህን የአቶ ጸጋዘአብ ካሳን ሀሳብ በሚያጠናክር መልኩ ስምምነቱ በትግራይ በአፈሙዝ ሳቢያ የሚሞት ወጣት ቢያስቀርም በረሃብ፣ በበሽታ የሚሞትን ግን አላስቀረም ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

እንደ አቶ ጸጋዘአብ ካሳ ገለጻ ሌላኛው ከምንም ነገር በላይ ስምምነቱ ያላሳካው ደግሞ ከአንድ ሚሊየን በላይ ተፈናቃይ ወደ ቤቱ አለመመለሱ መሆኑን አመላክተዋል። በጦርነቱ ሳቢያ የተፈናቀለው የክልሉ ነዋሪ አሁንም አስቸጋሪ ግዜያትን እንዲያልፍ ተገዷል ያሉት አቶ ጸጋዘአብ ካሳ ስንት በጋ እና ክረምት ተፈራረቀበት፤ ቢያንስ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ባለው አመት የተፈራረቀበትን ወቅቶች መመልከት በቂ ነው፤ ምንም ሳያገኝ፣ ወደ ቤቱ ሳይመለስ፤ ሌላ ደግሞ ግዛቱን የያዙ ሀይሎች ጭምጨፋውን እንደቀጠሉ መሆኑ፤ ሁሉንም ነገር ከልክለው እስካሁን ድረስ አፍነውታል፤ ከምንም ነገር በላይ ደግሞ ተፈናቅሎ ጥሎት በሄደው ቀየው ላይ የራሳቸውን ሰዎች አምጥተው ማስፈራቸው፤ ይሄ ይቀራል ተብሎ ነበር ተጠብቆ የነበረው። ይሄ አልሆነም ብቻ ሳይሆን ጭራሽ በከፋ መልኩ ቀጠለ ብለዋል

መምህር ገብረመድህን ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው የመመለሱ ሁኔታ ህልም ሁኖ ቀርቷል ሲሉ ገልጸው ይልቅስ ተጨማሪ ተፈናቃዮች ከስምምነቱ በኋላ በተለይ ከደቡብ እና ከምዕራብ ትግራይ  ቀያቸውን ለቀው መሰደዳቸውን በአብነት አስቀምጠዋል።

አዲስ ስታንዳር ያነጋገራቸው የክልሉ ፖለቲከኞች እና ሙሁራን ከተፈናቃዮች ጋር በተያያዘ በሰጡት አስተያየት የፕሪቶርያው ስምምነት በአንድ አመት እድሜው ያላሳካውን ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ እንቅፋት የሆነው በፌደራል መንግስቱ በኩል በስምምነቱ መሰረት የክልሉ የግዛት አንድነት ህገመንግስቱን መሰረት በማድረግ አለማስከበሩ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል። የፌደራል መንግስቱ የኤርትራ ሰራዊት እና የአማራ ሀይሎች ከያዟቸው የክልሉ አከባቢዎች እንዲወጡ አለማድረጉን በመጥቀስ ወቅሰዋል።

የባይቶናው ዶ/ር ጸጋዘአብ ካህሱ በስምምነቱ የአንድ አመት እድሜ በህገ መንግስቱ መሰረት የትግራይ ወሰኖች ይከበራሉ ብለው ጠብቀው እንደነበር አስታውሰው ይሄ አለመከበሩ ስምምነቱ በእንጥልጥል እንዲታይ፣ ወዴት እንደሚያመራ እንዳይታወቅ አድርጎታል ብለዋል። ይህም በሁሉም ወገን ጥርጣሬ እንዲሰፍን አድርጓል ሲሉ ገልጸዋል። የመቀለ ዩኒቨርስቲ መምህሩ ገብረመድህን በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በሰጡን አስተያየትየትግራይ የግዛት አንድነትና አስተዳደር ወደ ቦታው ሊመለስ ቀርቶ እንዲያውም ይበልጥ የጸጥታ እና አስተዳደራዊ መዋቅራቸውን ዘርግተው እየተጠናከሩ ነው፤ የተሻለ ሳይሆን የባሰ ነገር ነው የሆነው ብለዋል። 

ወደ ጦርነቱ የተገባው የፖለቲካ ልዩነቶች ተካረው መሆኑን ያወሱት የባይቶናው ዶ/ር ጸጋዘአብ ካህሱ ከስምምነቱ ያልተሳካው ሌላው ቁምነገር እነዚህ ፖለቲካዊ እና ወደ ጦርነቱ ያስገቡን ልዩነቶችን ለመፍታት ፖለቲካዊ ውይይት አለመጀመሩ ባሳለፍነው የፕሪቶርያው አንድ አመት የሰላም ስምምነት ወቅት ያልተሳካው ነው ባይ ናቸው። ስለዚህ ከስር መሰረቱ በሚፈታ መልኩ እነዚህ ጥያቄዎች ምንድን ናቸው፣ እንዴትስ መፈታት ይችላሉ ብሎ ወደ ፖለቲካ ውይይት አልተገባም ያሉን ዶ/ር ጸጋዘአብ አለመጀመሩ አሁንም የስጋት አደጋ እንዲያንዣብብ አድርጎታል፤ በማንኛውም ግዜ ሌላ መልክ ሊይዝ የሚችል መሆኑን፣ ስጋት መፍጠሩን አስታውቀዋል። የፖለቲካ ውይይቱ በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነትም መካተቱን ያወሱት የባይቶናው ዶ/ር ጸጋዘአብ ዋነኛ መነሻ ምክንያቶቹን ቁጭ ብሎ በጠረንጴዛ ዙሪያ በውይይት ለመፍታት አለመሞከሩ፣ በአቋራጭ መንገድ ለማድበስበስ እየተሞከረ መሆኑ፣ አደጋ እንዳለው አብራርተዋል።

ለመቀለ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ገብረመድህን በናይሮቢው የትግበራ ሰነድ የተካተተው እና የሰላም ስምምነቱ አካል የሆነው የስምምነቱ አንድ አካል የሆነውን ትጥቅ ማስፈታት፣ ተዋጊዎችን መበተን እና መልሶ ማቋቋም ሂደት (DDR) ጋር በተያያዘ መልሶ ማቋቋም ረጂም ግዜ ቢወስድም ቢያንስ ትጥቅ ማስፈታት እና ተዋጊዎች መበተን ብዙ ርቀት ይሄዳል የሚል እምነት እንደነበራቸው አውስተው ከትጥቅ ማስፈታት ውጭ ያለው አልተነካም ሲሉ ገልጸዋል። አጠቃላይ ሂደቱ አራት እና አምስት አመታት ሊወስድ እንደሚችል የጠቆሙን መምህሩ ረዝም ግዜ የሚወስደው ግን መልሶ የማቋቋሙን ነው፤ ተዋጊዎችን መበተን እና ትጥቅ ማስፈታት ግን በተነጻጻሪ በአጭር ግዜ ሊደረግ የሚችል ነው፤ ስለዚህም ጠብቄ ነበር ብለዋል። የመምህሩን ሀሳብ የባይቶናው ጸጋዘአብ ሆኑ የታሪክ ሙሁሩ ጸጋዘአብ ካሳ ለአዲሰ ስታንዳርድ በሰጡት ቃለምልልሰ እንደሚጋሩት አመላክተው የስምምነቱ አንድ አካል ከሆነውን ትጥቅ ማስፈታት፣ ተዋጊዎችን መበተን እና መልሶ ማቋቋም ሂደት (DDR) ተዋጊዎችን መበተን እና መልሶ ማቋቋም በአመቱ በስምምነቱ ካልተሳኩት መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ዶ/ር ጸጋዘአብ እስካሁን የትግራይ ህዝብን የሚወክል አካል በፌደራል መንግስቱ የለም፤ በተጨባጭ ትግራይ ከኢትዮጵያ ውጭ ነች፣ እንደዚህ ተሁኖ እስከመቸ ነው የሚዘለቀው ሲሉ ጠይቀው በጦርነቱ ሳቢያ ከፌደራል መንግስቱ የተገለለችው ትግራይ አሁንም የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ አመት ቢሆንም እንደተገለለች መሆኗን አስታውቀዋል። ይህም ያልተጠበቀ አቅጣጫ ሊፈጥር ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን አጋርተውናል።

ለስምምነቱ አለመሳካት ማን ነው ተጠያቂው?

የፕሪቶርያው ስምምነት በአንድ አመት እድሜው ካሳካው ይልቅ ያላሳከው እንደሚበዛ የገለጹልን የክልሉ ሙሁራን እና ፖለቲከኞች ስምምነቱ እንዳይሳካ ማን ነው እንቅፋት ብለን ጠየቅናቸው። ሁሉም ዋነኛ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ፈራሚዎቹ የፌደራል መንግስቱ እና ህወሓት መሆናቸውን አስታውቀው፣ ነገር ግን ሁለቱ እንቅፋት በመሆን የነበራቸው ሚና ሚዛን መቀመጥ እንዳለበት ጠቁመዋል፤ ለስምምነቱ መፈረም አስተዋጽኦ የነበራቸው እንደ አፍሪካ ህብረት ያሉት ተቋማትም ከተጠያቂነት እንደማይድኑ አመላክተዋል።

የባይቶናው ዶ/ር ፀጋዘአብ ለስምምነቱ አለመሳካት ማን ነው ተጠያቂ ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ ሲመልሱዋናው ሸክሙን መውሰድ ያለበት የፌደራል መንግስቱ ነው ብለዋል። የፌደራል መንግስቱ ሁለት ድርብ ሃላፊነት አለበት፣ እንደ የሀገር መንግስት ለዜጎቹ ማድረግ ያለበት ነገር አለ፣ ሌላ ደግሞ በውሉ መሰረት መፈጸም ያለበት ነገር አለ ሲሉ ገልጸው ስለዚህ ድርብርብ ሃላፊነት ያለው ፌደራል መንግስቱ የትግራይ ህዝብ ህዝቤ ነው የሚለው ከሆነ፣ ትግራይ የአገሪቱ አካል ነች ብሎ የሚያስብ ከሆነ አለመፈጸሙ ሊያመው ይገባ እንደነበር ጠቁመዋል። ህወሓትም ከተጠያቂነት አያመልጥም፣ ተጠያቂ ነው ብለዋል።

መቀለ ዩኒቨርስቲ መምህሩ ገ/መድህን ገ/ሚካኤል ለስምምነቱ አለመሳካት ተጠያቂዎቹየፌደራል መንግስቱ እና ህወሓት በመሆናቸውን ገልጸው የስምምነቱ አንድ አካል ከሆነውን ትጥቅ ማስፈታት፣ ተዋጊዎችን መበተን እና መልሶ ማቋቋም ሂደት (DDR) ጋር በተያያዘ ግን ከህወሓት ይልቅ ላለመሳካቱ የፌደራል መንግስቱ እና ድጋፍ ሰጪዎቹ አካላት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ ብለዋል።

የስምምነቱ አንድ አካል የሆነውን ትጥቅ ማስፈታት፣ ተዋጊዎችን መበተን እና መልሶ ማቋቋም ሂደት (DDR) ውስጭ ተዋጊዎችን ለመበተን እና መልሶ ማቋቋም ትግበራ የፌደራል መንግስቱ እና አደራዳሪዎቹ ወይም ደጋፊዎቹ የሚጠበቅ የባጀት ድጋፍ በማምጣቱ ላይ ሚናቸው ከህወሓት እንደሚልቅ ጠቁመው ህወሓት ተጠያቂ አይደለሁም ቢል ውሃ ይቋጥራል ሲሉ በአብነት አስቀምጠዋል። ህወሓት ከዲዲአሩ ሊጠየቅበት የሚችለው በትጥቅ መፍታቱ ላይ ያልፈጸመው ካለ ነው፣ ይህም በአፍሪካ ህብረት ታዛቢዎች ጭምር 90 በመቶ አስረክቧል መባሉን ጠቅሰዋል። ምናልባት የፌደራል ምንግስቱ ያላሳካው በስምምነቱ ወቅት ለዲዲአሩ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡ አካላት ስላልደገፉት ሊሆነም ይችላል፤ ይህም መታየት አለበት ብለዋል።

በዋነኝነት የትግራይ ተደራዳሪዎች ያላሳኩተ ነገር አለ ከተባለ ከአቅም ማጣት ጋር የተያያዘ ይመስለኛል ያሉን መምህሩ የክልሉ መንግትስ ለሰራተኛው እንኳ በቅጡ ደመወዝ መክፈል የማይችል ለዲዲአሩ የገንዘብ አቅም የሚኖረው አይመስለኝም ብለዋል።

እዚህ ላይ በታወቅ ያለበት ይላሉ መምህር ገብረመድህን ገ/ሚካኤል የስምምነቱ አንድ አካል ከሆነውን ትጥቅ ማስፈታት፣ ተዋጊዎችን መበተን እና መልሶ ማቋቋም ሂደት (DDR) የፌደራል መንግስቱ ዋነኛ ፍላጎት እና ማሳካት የፈለገው ትጥቅ ማስፈታቱን ስለሆነ አሳክቶ ሌሎቹን ትቷል የሚል እምነት ነው ያለኝ፤ ያለ ሂደት ታጣቂዎቹ ወደ ህብረተሰቡ ቢቀላቀሉ ዋነኛው ተጎጂው ክልሉ ነው፣ በተለይ ህወሓት፤ እንዲሁ ቢቆዩም ተጎጂው በተመሳሳይ ህወሓት እና ትግራይ ነች፤ በህወሓት ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳደራል። ታጣቂዎቹ በቀጥታ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ግንኙነት ስለማይኖራቸው ዋነኛው ፍጥጫ የሚፈጠረው በሰራዊቱ እና በህወሓት ላይ ይሆናል። ለዚህ ነው ፌደራል መንግስቱ ብዙም የማይገፋበት። የአፍሪካ ህብረትም ይሁን ሌሎቹ ታዛቢዎች ገለል ያሉ ይመስላል ብለዋል።

ከስምምነቱ ማን አተረፈ? ማንስ ከሰረ?

አንድ አመት በሞላው የፕሪቶርያው ስምምነት ማን ምን አተረፈ ብለን ብናስቀምጥ ምላሹ ምን ይሆናል ስንለ የጠየቅናቸው የመቀለ ዩኒቨርስቲው የፖለቲካ ሳይንሰ መምህሩ ገ/መድህን ገ/ሚካኤል ፌደራል መንግስቱ ሙሉ በሙሉ አትርፏል የሚል አስተያየት ነው ያለኝ ብለውናል። መምህር ገብረመድህን በማሳያነትም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ በፌደራል መንግስቱ ላይ የነበሩ ጫናዎች መቀነሳቸውን፣ የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ ጫናዎች እና ማዕቀቦች በስምምነቱ ምክንያት ባሳለፍነው አንድ አመት መቃለላቸውን ጠቅሰዋል። ሌላኛው የፌደራል መንግስቱ የስምምነቱ ትርፍ በሂደት አደራዳሪዎቹን ማስወጣቱ ወይንም ከእይታ ውጭ ማድረጉ መሆኑን ጠቁመዋል። አሁን ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ፌደራል መንግስቱ ስምምነቱን በእጁ ጠቅልሎ ይዞታል ብለዋል።

የትግራይ መንግስት ምን አተረፈ ብትለኝ፣ እርግጠኛ አየደለሁም ስምምነቱ ባይኖር ሊፈጠር የሚችል ኪሳራ አስቀርተናል የሚለው ፕሮፓጋንዳቸውን ነው ያሉን መምህሩ በትግራይ በኩል እንዲሟሉ ሲጠየቁ የነበሩት ነገሮች አለተመለሱም ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። በማሳያነትም ተፈናቃዩ አልተመለሰም፣ የክልሉ የግዛት አንድነት አልተከበረም ሲሉ ገልጸዋል። ህወሓት በስምምነቱ በረሃብ እና በበሽታ የሚሞት የክልሉን ህዝብ ማስቀረት አልቻለም፤ ጥይት የሚሞቱትን ግን አስቀርቷል የህወሓት ስኬት ይሄ ነው ብለውናል።

የትግራይ ህዝብ ወደ ተሟላ የልማት እንቅስቃሴ ይገባል የሚል ተስፋ ነበረኝ፣ እሱም ምንም የተጀመረ ነገር የለም፤ እንዲሁ በግለሰቦች የሚንቀሳቀሱ ሱቆች እና ድርጅቶች ማለትም አስቤዛ ከመገባት ያለፈ የልማት እንቅስቃሴዎች የሉም ብለዋል። ኦዲት ቢደረግ ትግራይ ካተረፈው የከሰረው ይበዛል ሲሉ አመላክተዋል።

የአቶ ጸጋዘአብ ካሳ በበኩላቸው ዋነኛው አትራፊ የፌደራል መንግስቱ መሆኑን አመላክተው ማዕከላዊ መንግስቱ በጦርነት ያጣውን በሰላም ሂደቱ በፖለቲካ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ብቻ ምን ያክል የስምምነቱ አትራፊ መሆኑን ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል። በስምምነቱ መሰረት ማሟላት የሚገባውን ነገር ሁሉ ባለማሳካት ለሚፈልገው አላማ እና ግብ መጠቀሚያ እያደረገው ነው ሲሉ ተችተዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button