ዜናህግ እና ፍትህ

ዜና፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ በመርዓዊ የተፈጸመውን ግድያ ሊመረምር መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8/ 2016 ዓ/ም፦ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመርማሪ ቦርድ በመርዓዊ ከተማ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከህግ ውጭ ግድያ መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሪፖርቱ ማሳወቁን ተከትሎ ምርመራ ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያካቲት 5፣ 2016 ዓ/ም ባወጣው ሪፖርት በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን በመራዊ ከተማ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና ፋኖ ታጠቁ ኃይሎች መካከል ውጊያ መካሄዱን ተከትሎ፣ ቢያንስ 45 ሲቪል ሰዎችን በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ተገድለዋል ብሏል። 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመርማሪ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ነጃት ግርማ፤ በመራዊ ተፈጽሟል የተባለውን ግድያ  ቦርዱ ወደ ስፍራው በማቅናት ምርመራ እንደሚያደርግ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ሰብሳቢዋ ጉዟቸው መቼ እንደሚሆን ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

ኢሰመኮ በሪፖርቱ እንዳስታወቀው፣ በመራዊ በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎቹ ከሕግ ውጭ የተገደሉት ሰዎች “ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል” በሚል ምክንያት ነው። በተጨማሪም “የፋኖ አባላት ናቸው” በሚል ተጠርጥረው የተያዙ እና ለጊዜው ብዛታቸውን ለማረጋገጥ ያልተቻለ ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ መገደላቸውን ማረጋገጡን ኮሚሽኑ አክሎ ገልጿል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ የሰጡት የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በተጠቀሰው ዕለት በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ መካከል ግጭት እንደነበር አርጋግጠው “ሲቪሎችን ዒላማ ያደረገ ርምጃ በመንግሥት ኃይሎች አልተፈጸመም” ሲሉ ውንጀላውን አስተባብለዋል፡፡

መከላከያ ሠራዊቱ ርምጃ የወሰደው፣ “ጥቃት በፈጸሙበት ጽንፈኛ ኃይሎች ላይ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ፣ ታጣቂዎቹ  “በተለያዩ አቅጣጫዎች መከላከያ ሠራዊቱ የሰፈረበትን ካምፕ በማፈን መሣሪያ እና ሎጂስቲኩን ለመዝረፍ በመንቀሳቀሳቸው ራሱን የመከላከል መብቱን ተጠቅሞ ነው እርምጃ የወሰደው” ሲሉ ተናግረዋል

በመራዊ የተፈጸመውን ግድያ አመልክቶ ዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ ህብረት “ሙሉ ምርመራ” እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። የካናዳ እና አሜሪካ መንግስትም ድርጊቱ አንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በጉዳዩ ላይ ምርመራ የሚያደርግ “ሌላ አካል” እንደማይኖር እና ጉዳዩ የሚመለከተው በአማራ ክልል የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ እንደሆነ ተናግረዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመርማሪ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢዋ ዶ/ር ነጃት ግርማ ግድያው ከተፈጸመ ሁለት ሳምንት በማለፉ ለምርመራ አልዘገያችሁም? ተብለው በቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምክትል ሰብሳቢዋ፤ በሚዲያ ዘገባዎች እንደማይወሰኑ እና “ጥቆማዎችን እንዲሁም ይፋዊ የሆኑ ሪፖርቶችንም እንጠብቃለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። በተጨማሪም የቦርዱ የሥራ ጊዜ በቅርቡ መራዘሙን ገልጸው ምርመራዎችን ማካሄድ ቢፈልጉም መሬት ላይ ወርደው ለመመርመር ግን በፀጥታው ሁኔታ እንደሚወሰን ምላሽ ሰጥተዋል።

በክልሉ ባለው የፀጥታ ሁኔታ መርማሪዎቻቸው ጥሰቶች ተፈጽመዋል በተባሉ ሌሎች አካባቢዎች ተጉዘው ለመመርመር እንደተቸገሩም ዶክተር ነጃት አስረድተዋል። 

አሳሳቢነቱ በቀጠለው በአማራ ክልል የትጥቅ ግጭት ምክንያት ባሳለፍነው ጥር ወር ብቻ በመራዊ የተፈጸመውን የሲቪል ሰዎች ግድያ ጨመሮ ከ 66 በላይ ሲቪል ሰዎች “በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ” መገደላቸውን ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሪፖርት መረዳት ተችሏል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button