ዜናፖለቲካ

ዜና፡ ኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ያደረጉትን ንግግር “የተሳሳተ” እና “መረጃ የጎደለው” ስትል ተቃወመች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 9/2016 ዓ/ም፦ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ከትናንት በስቲያ ያደረጉትን ንግግር “የተሳሳተ” እና “መረጃ የጎደለው”  ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቃውሟል።  

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትላንት ባወጣው መግለጫ የአምባሳደሩ ንግግር “የኢትዮጵያ መንግስት ሀገሪቷን እንዴት መምራት እንዳለበት ያልተጠየቀ ምክር ለመምከር የሞከረ ነው” ሲልም ገልጿል፡፡

ሚኒስቴሩ ይህን ያለው በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ከትላንት ብስቲያ ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም በአሜሪካን ግቢ በሀገሪቱ ወቅታዊ የደህንነት ሁኔታ፣ በሀገራዊ ምክክሩ እና በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ ነው። 

አምባሳደሩ በመግለጫቸው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን እና የፋኖ ታጣቂዎችን ጨምሮ በረካታ የታጠቁ ኃይሎች ከመንግስት ጋር እየተዋጉ መሆኑን ገልጸው ጊዜያዊ ሀገር አቀፍ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

ያለምንም ፍርድ ግድያ፣ የዘፈቀደ ጅምላ እስር፣ እገታ፣ በግጭት ጋር የተያያዘ ጾታዊ ጥቃቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ባፋጣኝ፣ ትኩረት ተሰጥቷቸው፣ ተጠያቂነትን ባሰፈነ መልኩ፣ እውነተኛ በሆነ ግልጽነት ባለው የሽግግር ፍትህ ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።

አምባሳደሩ ባደረጉት ንግግር “በምርጫ ወደ ስልጣን የመጣን መንግስት እንጥላለን በሚል የሚንቀሳቀሱ፣ ንጹሃንን ከሚያግቱና ከሚያሸብሩ አካላት ጋር መንግስትን ያነሳ ነው” ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስጋቱን ገልጿል።

የአምባሳደሩ መልዕክት ከሁለቱ ሀገራት ታሪካዊና ወዳጅነት ላይ ከተመሰረተው ግንኙነት የተቃረነ እንደሆነም ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በአዲስ አበባ ከሚገኘው ኤምባሲ ጋር በመስራት የተፈጠረውን ስህተት እንዲታረም የሚያደርግ መሆኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል። ኢትዮጵያ በመከባበር ላይ የተመሰረተ የሁለትዮሽ ግንኙነትና ትብብር እንዲኖር ቁርጠኛ መሆኗንም መግለጫው አረጋግጧል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button