ህወሓት መልሶ ህጋዊ እንዲሆን የሚያስችል አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23/2016 ዓ.ም፡- የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባ በአራት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን አስታወቀ።

በሙሉ ድምጽ ለተወካዮች ምክር ቤት ከተላኩ ጉዳዮች መካከል ከህጋዊ እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውጪ የቆዩ እንደ ህወሓት ያሉ የፖለቲካ ቡድኖች መልሶ መመዝገብ የሚያስችል ረቂቅ የአዋጅ ይገኝበታል።

ከጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅን ለማሻሻል በቀረበ አዋጅ ላይ መሆኑን ጠቁሟል።

ከህጋዊ እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውጪ የቆዩ የፖለቲካ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ እነዚህን አካላት ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ አድርጎ ለመመዝገብ የሚያስችል ስርዓት በነባሩ አዋጅ ላይ አለመካተቱን አውስቷል።

ምክር ቤቱ በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ እና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ መልሶ መመዝገብ የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት ረቂቅ የአዋጅ ማሸሻያ ተዘጋጅቶ መቅረቡን አስታውቋል።

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን አመላክቷል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የካቲት 5 ቀን 2016 ቀን ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የህወሓትን ተመልሶ በምርጫ ቦርድ እውቅና ስለማግኘት ተጠይቀው በሰጡት ምላሻቸው የፌደራል መንግስት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ እንደማይደግፈው መግለጻቸው ይታወሳል።

በአዲስ አበባ ከፌደራል መንግስቱ ጋር በነበራቸው ውይይት “ህወሓት እያሉ መግለጫ እያወጡ ህወሓት የሚባል አናውቅም የሚል ንግግር ሊኖር አይችልም” መባሉን በወቅቱ አስታውቀዋል።

“ያሉትን የህግ እንቅፋቶች ቶሎ በማሰቀረት ህወሓት ህጋዊ ህልውናው የሚረጋገጥበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት ተረዳድተናል፤ የፍትህ ሚኒስቴር ጉዳዩን እንዲከታተለው እና ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ ሃላፊነቱ ተሰጥቶታል” ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል። በአጭር ግዜ ውስጥ ይፈጸማል ማለታቸውም በዘገባው ተካቷል።

በመቀጠልም ምክር ቤቱ የተወያየው በንብረት ማስመለስ አዋጅ ላይ መሆኑን ጠቁሞ በተለያዩ አዋጆች ውስጥ ተበታትነው ያሉትን የንብረት ማስመለስ እና አስተዳደር ድንጋጌዎች በአንድ ወጥ ሕግ ውስጥ በማካተት ለአፈጻጸም ምቹ የሆነ ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ መቅረቡን አስታውቋል።

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው በህገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አድርጎ ስለማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቀረበው አዋጅ ላይ መሆኑን ገልጿል።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የነዳጅ ውጤቶችን የግብይት ሥርዓት ለመደንገግ በቀረበው አዋጅ ላይ መሆኑን የጠቆመው የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ  የነዳጅ ውጤቶች ከአስመጪ ጀምሮ እስከ ተጠቃሚዎች ድረስ ያለው ግብይት ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ ፍትሐዊ እና ተደራሽ የሆነ የአቅርቦት ሰንሰለት እና የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ መቅረቡን በመግለጽ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን አስታውቋል።

Exit mobile version