ክልሎች ለተረጂዎች የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ 70 በመቶው እራሳቸው እንዲያቀርቡ የፌደራል መንግስቱ ወሰነ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22/2016 ዓ.ም፡- በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የአደጋና ስጋት አመራር ኮሚሽኖች በየክልሎቻቸው መሬት በመውሰድ አምርተው እርዳታ የሚፈልጉ ዜጎችን እራሳቸውን ችለው እንዲረዱ እንደተነገራቸው ተገለጸ።

ክልሎች ዜጎች ሲፈናቀሉባቸውም ሆነ ድርቅ ሲያጋጥማቸው የሚረዱት ምግብ እንዲያመርቱ ከዚያም ባለፈ በጀት መድበው እንዲያቀርቡ አቅጣጫ መቀመጡን አዲስ ስታንዳርድ የደረሰው መረጃ ያሳያል።

አቅጣጫው የተቀመጠው በተያዘው በጀት አመት ጥቅምት ወር ላይ የሀገሪቱ የአደጋ ስጋት ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ መሆኑም ተጠቁሟል፤ ክልሎች በተለያዩ ምክንያቶች ለዜጎቻቸው የምግብ እርዳታ ማቅረብ ቢያስፈልጋቸው 70 በመቶ እራሳቸው እንዲሸፍኑ፣ ቀሪው 30 በመቶ ደግሞ ፌደራል መንግስቱ እንዲያግዝ ስምምነት ተደርሷል ተብሏል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ከክልል የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነሮች ጋር በመሆን ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም በበየነ መረብ ባካሄደው ውይይት “የሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም“ ለማካሄድ የተከናወኑ ተግባራትን መገምገሙን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የኮሚሽኑ መረጃ እንደሚያሳየው መንግስት ክልሎች በራሳቸው አቅም ተረጂዎቻቸው እርዳታ እንዲያቀርቡ እየተደረገ ያለው የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ መጽደቁን ተከትሎ ነው።

በምክትል ጠ/ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሚመራው የአደጋ ስጋት ም/ቤት ፤ “የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ መጽደቁን ተከትሎ “ከተረጂነት እንውጣ” የሚል አብዮት ቅስቀሳ ተጀምሮ ሁሉም የክልል ከፍተኛ መንግስታት እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር አመራሮች የሚመሩት ንቅናቄ ተፈጥሯል” ብሏል፡፡

ኮሚሽኑ ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም በበየነመረብ ያካሄደው ውይይት ዋነኛ አላማ “ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም ለመመለስ” የሚስችላቸውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ምን ደረጃ እንደደረሱ ለመስማትና የድጋፍና ክትትል ሥራዎችም ካሉ ለመደገፍ ያለመ መሆኑን ጠቁሟል።

የክልል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነሮችም የተረጂነትን አመለካከት መቀልበስ፤ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፤ ምግብና ምግብ ነክ ክምችቶችን ለመያዝና ለማጠናከር እያከናወኗቸው ያሉትን ተግባራት በዝርዝር በሪፖርታቸው አቅርበዋል ያለው የኮሚሽኑ መረጃ የገጠሟቸውን ተግዳሮቶችም እና ያሉትን ምቹ አጋታሚዎች አንስተው ውይይት እንደተደረገባቸው አስታውቋል።

መንግስት ወደዚህ ውሳኔ የገባው በዋናነት ከውጭ የሚገኘው እርዳታ እየቀነሰ በመምጣቱ መሆኑን በወቅቱ መገለጹን የኦሮምያ ክልል የቡሳ ጎኖፋ ሃላፊ ሞገስ ኢዳኤ ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋግጠዋል። በተጨማሪም “በሀገሪቱ በተለያዩ ምክንያቶች በተለይም በተፈጥሮ አደጋ እና ግጭት የሚፈናቀለው ስለበዛ ክልሎች ተሳትፎ እንዲያደርጉ ተወስኗል” ብለዋል።

የእርዳታ አቅርቦቱን “70 በመቶ ክልሎች እንዲሸፍኑ፣ ቀሪው 30 በመቶ ደግሞ ፌደራል መንግስቱ እንዲያግዝ ስምምነት ተደርሷል” ያሉን ሃላፊው “በዚያ አቅጣጫ እየሄድን ነው፣ በኛ ክልል ሀብት ሞቢላይዝ የማድረግ ስራ እየሰራን ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ክልሎች 70 በመቶው ከየት ያመጡታል

ክልሎች 70 በመቶ የሚሆነውን እርዳታ እንዴት ሊያገኙ ይችላሉ ተብሎ ታሳቢ ተደረገ ስንል የጠየቅናቸው ሞገስ ኢዳኤ በዋናነት እንደተቋም ከክልሉ መሬት ጠይቀን በመውሰድ አርሰን በማምረት ነው ብለዋል።

ማረስ ያለብንን መሬት መጠን ፌደራል መንግስት እቅድ አውጥቶ ለእያንዳንዱ ክልል ማከፋፈሉን አስታውቀዋል።

ለትግበራው የየክልሎቹ ሴክተሮች እገዛ እንደሚያደርጉ በአቅጣጫው መቀመጡን የጠቆሙልን ሃላፊው ሞገስ “ግብርና ቢሮ ያግዘናል፣ ምርጥ ዘር ያግዘናል በነዚህ አካላት ጋር ተጋግዘን በራሳችን ነው አርሰን የምናመርተው” ሲሉ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ፈንድ አለን ትራክተሮች አወዳድረን በኪራይ እየወሰድን ባለሞያም መድበን እርሻውን እናከናውናል ብለዋል።

በእርሻ ከሚሰበሰበው ለእርዳታ ከሚሆነው ምርት በተጨማሪ ለተረጂዎች ክልሎች በጀት እንዲመድቡ አቅጣጫ መቀመጡን የነገሩን ሞገስ ለዚህ ተግባር የሚውል ሀብት የማሰባሰብ ይሰራሉ ብለዋል

ከውጭ ሀገራት እና ተቋማት ድጋፍ እና እርዳታ ማሰባሰብ የፌደራል መንግስቱ ድርሻ ነው። ከክልል ማለፍ ህጉ አይፈቅድልንም ሲሉ አብራርተዋል።

የኦሮምያ ተሞክሮ

የፌደራል መንግስቱ ይህንን አቅጣጫ ለሁሉም ክልሎች ከማስቀመጡ በፊት ነው የኦሮምያ ክልል ይህንን አካሄድ የተገበረው ሲሉ ያመላከቱት ሀላፊው፤ ቦሳ ጎኖፋ የተሰኘው የኦሮሞ ማህበረሰብ የቆየ ትውፊት ስላለ እሱን ነው የተገበርነው ሲሉ አብራርተዋል። በዚህም መሰረት አባላት አፍርተናል  አሁን እያናገርኩህ እስካለበት ሰዓት ድረስ 24 ሚሊየን ደርሷል ሲሉም ገልጸዋል።

ከዚህ ከፍተኛ ቁጥር ካለው አባለት በየወሩ መዋጮ እንደሚሰበሰብ ጠቁመው ከዚህ በተጨማሪ ስጦታዎች እናሰባስባለን፣ መለገስ ከሚፈልጉ አካላት ሀብት እናሰባስባለን ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ኦሮምያ በክልሉ በሚገኙ 21ዱ ዞኖች በክረምቱ ወራት መጋዘኖች እንገነባለን ሲሉ ጠቁመው ከሚገኘውን ምርት በመጠባበቂያነት እናስቀምጣለን፤ ችግር ሲደርስ ከእነዚህ ክምችቶች በማንቀሳቀስ የመደገፍ ስራ እንሰራለን ሲሉ ቀጣይ አሰራራቸውን አመላክተዋል።

ክልሎች መቼ እንዲጀምሩ ነው አቅጣጫ የተቀመጠው

አቅጣጫው ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ስንል የጠየቅናቸው የኦሮምያ ክልል ቦሳ ጎኖፋ ሃላፊ ሞገስ እንዳስታወቁት ስምምነት ላይ የተደረሰው በጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም መሆኑን ጠቁመው በጋውን በሙሉ ሁለቱም አካላት ለመተግበር ሲሞክሩ እንደነበር ለአዲስ ስታንዳርድ አመላክተዋል።

70 በመቶ እና 30 በመቶ የሚለው ተግባራዊ ባይደረግም፣ ክልሎች ከበጀታቸው በጀት እየመደቡ አቅርቦት ነበራቸው ሲሉ ጠቁመው 70 በመቶ እና 30 በመቶ የሚለውን አሟልተናል ማለት አንችልም ሲሉ እንደክልል የአመቱን ክንውናቸውን ገልጸዋል።

ዘንድሮ ባናሟላም በሚቀጥለው ግን ክልሎች የሚጠበቀውን ምርት የሚያመርቱ ከሆነ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን ያህል ማምረት እንችላል፤ ወደ ክልላችን የሚገባውን የእርዳታ እህል ያክል ማምረት የሚያስችለን መሬት ነው የጠየቅነው፤ በዚህም 70 በመቶ እና 30 በመቶ የሚለው ይፈጸማል ሲሉ አስታውቀዋል። አስ

Exit mobile version