ዜና: በአንካራ የተገናኙት ኢትዮጵያ እና ሶማልያ “ልዩነታችንን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ ነን፣ በድጋሚ በነሃሴ ወር ተገናኝተን እንመክራለን” አሉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25/2016 ዓ.ም፡- በቱርክ መንግስት አመቻችነት በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ትላንት ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም በአንካራ ሲካሄድ የነበረው ድርድር መጠናቀቁ ተገለጸ። “ልዩነታችንን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ ነን፣ በድጋሚ በነሃሴ ወር ተገናኝተን እንመክራለን” ሲሉም አስታውቀዋል።

ድርድሩን አስመልክቶ የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊደን ትላንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ ድርድሩ በመልካም ሁኔታ ተካሂዷል ከማለት በስተቀር የገለጹት ውጤት የለም።

“ጥሩ ውይይት ተደርጎበታል” ሲሉ የቱርኩ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የገለጹት የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ድርድር “በቀጣይ ነሃሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም በድጋሚ ተገናኝተው ለመወያየት” ቀጠሮ በመያዝ መጠናቀቁን አመላክተዋል።

“ውይይቱን በማስቀጠል ልዩነቶቻቸውን በንግግር ለመፍታት እና የቀጠናውን ሰላም ለማስጠበቅ ስምምነት ላይ ደርሰዋል” ሲሉ  የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊደን ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።

ቱርክ እየተጫወተችው ያለው ሚና የአመቻችነት ነው ሲሉ ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞቹ ገልጸዋል።

“በጉዳዩ ላይ ባሉ ብዙ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችና ውስብስብ ተፈጥሯዊ ምክንያት ሳቢያ በጉዳይ ዙሪያ ተጨማሪ ማሰላሰሎች እንደሚያስፈልገን ምስጢር አይደለም፤ ዛሬ በነበረው ውሎ በሰማነው ነገር ተስፋ ሰንቀናል” ሲሉም ገልጸዋል።

በአንካር ይፋ የተደረገው የሶስቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የጋራ መግለጫ ላይ እንደተጠቀሰው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ልዩነታቸውን በሚመለከት ግልጽ፣ ቅንነት የተሞላበት እንዲሁም የመጻኢ ግዜያትን ታሳቢ ያደረገ ውይይት በተናጠል ማድረጋቸውን ጠቁሟል።

የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል ያለው የጋራ መግለጫው የቱርክ ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን ውይይቱ እንዲደረግ በማመቻቸታቸው ምስጋና አቅርበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የድርድሩን መጠናቀቅ ተከትሎ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን መግባቢያ ሰነድ ለመሻር ምንም አይነት ምልክት አላሳየችም ሲሉ ተደምጠዋል። “ ኢትዮጵያ ከያዘችው መስመር የመመለስ ፍላጎት አላሳየችም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ድርድሩ እንዲካሄድ የጠየቀችው ኢትዮጵያ ነች፣ ሁለቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ፊት ለፊት ተገናኝተው አልመከሩም በቱርክ በኩል እንጂ ሲሉ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድ ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ለማርገብ ያለመ ንግግር ለማድረግ የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ቱርክ መግባታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ትላንት ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በተደረገው ውይይት ሀገራቱን በመወከል የተሳተፉት የሁለቱ ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒትሮች መሆናቸው በዘገባው ተካቷል።

ድርድሩ የተመራው በሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ ፊቅ እና በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በተመሩ ልዑካን መሆኑም ተጠቁሟል። አስ

Exit mobile version