ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በሰላማዊ ሰልፍ ሽፋን በአዲስ አበባ የሽብር ተግባር ሊፈጸም ነበር ሲል መንግስት ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 27/2016 ዓ.ም፡- በአዲስ አበባ በሰላማዊ ሰልፍ ሽፋን ሁከትና የብጥብጥ ለመፍጠር የሞከሩ ቡድኖችን ተግባር አከሸፍኩ ሲል መንግስት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል ዛሬ ህዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም ማምሻውን ባወጣው መግለጫ “በሰላማዊ ሰልፍ ሽፋን አዲስ አበባን የሁከትና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ የሽብር ተልዕኮ ተቀብለው በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖች ሴራ አክሽፊያለሁ” ሲል ገልጿል።

“የሽብር ተልእኮውን” የተቀበሉት እና በቁጥጥር ስር የዋሉት ቡድኖች “በትጥቅ የታገዘ ግፍና ግድያ በመፈፀም በኦሮምያ እና የአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ከውጭ ሀይሎች ጋር በመተባበር ነው” ሲል ገልጿል።

“አንዳንድ የውጭ ኃይሎች በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በአንዳንድ አካባቢዎች የሕዝቡን ሰላም እያወኩ ያሉ ጽንፈኛ ኃይሎችንና ሽብርተኛውን ሸኔን እየደገፉ ሀገርን ለማፍረስ እያደረጉ ያለውን እኩይ ሴራ ግብረ -ኃይሉ ደርሶበታል” ብሏል መግለጫው።

እነዚህ ፅንፈኛ ኃይሎች እና የሽብር ቡድኖች በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በአንዳንድ አካባቢዎች እየፈፀሙት ያለውን ፀረ- ሰላም እንቅስቃሴ ወደ አዲስ አበባም በማስፋፋት በሚፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ሀገሪቱን የትርምስ ቀጣና እናደርጋለን በማለት የጥፋት ሴራዎችን አቅደው በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ በተደረጉ የመረጃ ስምሪቶች ተረጋግጧል ብሏል መግለጫው፡፡

በዚህ መነሻነትም ወደ ከተማዋ :የታጠቁ ኃይሎችንና ቡድኖችን አስርጎ የማስገባት ሙከራ ያደረጉ ሲሆን፤ ሰልፍ አናካሂዳለን በሚል ሰበብና ሽፋን ሁከትና ግርግር በመፍጠር ንፁሃንን ኢላማ ያደረግ የሽብር ጥቃት የመፈፀም የተጠና ዕቅድ ይዘው ሲንቀሳቀሱ” እንደነበር መታወቁን የጋራ ግብረ -ኃይሉ መግለጫ አመልክቷል፡፡ ይሄንን “እኩይ የጥፋት ሴራ ለመፈጸም ተልዕኮ የወሰዱ 97 ተጠርጣሪዎች በተከናወኑ ኦፕሬሽኖች በቁጥጥር ስር” መዋላቸውንም አስታውቋል፡፡

የጋራ ግብረ- ኃይሉ በመግለጫው “መንግሥት በሀገሪቱ ብሎም በመዲናይቱ አዲስ አበባ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ” ጠቁሟል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

መግለጫው አክሎም፤ “የአማራ ክልል ጽንፈኛ ኃይሎች እና የሸኔ የሽብር ቡድን ታጣቂዎችን ሴራ ለማክሸፍ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የተቀናጀ ፣ጠንካራና ድንገተኛ ፍተሻ መካሄዱንና ከእነዚህ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ጋር በትብብር የሚሠሩ ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር እንዲውሉ” መደረጉን አመልክቷል፡፡

ለጊዜው የተሰወሩ ተጠርጣሪዎችን አድኖ ለመያዝም የተቀናጀ ክትትልና ስምሪት እየተከናወነ መሆኑን ገልጿል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተካሄደ ድንገተኛ ፍተሻም “ሰርገው ወደ ከተማዋ ከገቡ ፅንፈኞችና የሸኔ ሽብር ቡድን አባላት በርካታ የጦር መሣሪያዎች፣ ተቀጣጣይ ፈንጂዎች፣ ቦንቦችና የሬዲዮ መገናኛዎችም” ጭምር መያዛቸውን አስታውቋል፡፡

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button