ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ የኢሬቻ በዓል ሲከበር በዋለበት ሁለት ቀናት በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሁለት ወረዳዎች ላይ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት ከ12 በላይ ሰዎች ተደገሉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1/ 2016 ዓ.ም፡- የኢሬቻ በዓል በተከበረበት ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን፣ ሃባቦ ጉዱሩ እና ኮምቦልቻ ወረዳዎች ላይ በተፈፀመ የድሮን /የአየር ጥቃት ከ12 ሰዎች በላይ መገደላቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ተናገሩ፡፡

ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የሃባቦ ጉዱሩ ወረዳ ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንገለፀው፣ በወረዳው ልዩ ስሙ መርፈታ መኮንን በሚባል አካባቢ ቅዳሜ መስከረም 26 ቀን መንግስት “ሸኔ” ብሎ የሚጠራው እራሱን ኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት የሚለው ታጠቂ ሀይል እና በመንግስት ሀይሎች መካከል ሲካሄድ በነበረ ግጭት ላይ መንግስት ረፋድ 5፡30 በፈፀመው የድሮን ጥቃት 7  የወረዳው ነዋሪዎች ሞተዋል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የሃባቦ ጉዱሩ አጎራባች በሆነው የኮምቦልቻ ወረዳ ነዋሪ በበኩሉ በሁለቱ ወገኖች መካከል ሲካሄድ የነበረው ግጭት በማግስቱ መስከረም 27 መቀጠሉን ገልፆ በእለቱ ከሰዓት በኋላ 10፡30 ላይ ልዩ ስሙ ለገ ኮምቦልቻ በሚባል ስፍራ መንግስት በፈፀመው የአየር ጥቃት 5 ሰዎች ወድያው ሲሞቱ ሶስት ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በመድረሱ ወደ ኮምቦልቻ ሆስፒታል ተወስደው ህክምና ላይ ናቸው ሲል ተናግሯል፡፡

በተጨማሪም በእለቱ ረፋድ 4፡30 ላይ የመንግስት ሀይሎች በወረዳው በሚገኘው ሁላ ጉቶ ቀበሌ ውስጥ በከፈቱት ተኩስ ሁለት ወጣቶች እና አንድ አዛውንት መገደላቸውን ነዋሪው አክሎ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጧል፡፡

ኮምቦልቻ ወረዳ ከኮምቦልቻ ከተማ በ10 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ቢቂልቱ ባርገሞ ሞሴ የሚባል ቦታ ላይ የምንግስት የፀጥታ ሀይሎች በከፈቱት ተኩስ ፍቃዱ አበራ የተባለ የአካባቢው አርሶ አደር በጥይት ተመቶ ጉዳት እንደደረሰበት እና መኖሪያ ቤቱ መቃጠሉን ለላኛው የወረዳው ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ አስረድቷል፡፡ ነዋሪው አክሎም በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት እና በመንግስት ሀይሎች መካከል ያለው ግጭት መስፋፋቱን ተከትሎ የስልክ እና የማብራት አገልግሎት መቋረጡን ገልጧል፡፡

መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ የመንግስት የፀጥታ ሀይሎች እና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት በአሁኑ ወቅት መባባሱን የተናገሩት ነዋሪዎቹ በዚህም ምክንያት በተለይ ባለፉት ቀናት ውስጥ በኮምቦልቻ እና ሃባቦ ጉዱሩ ወረዳዎች የበርካታ ዜጎች ህይወት እያለፈ እና በርካታ ነዋሪዎች ከቀያቸው እየተፈናቀሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በምዕራብ ኦሮሚያ በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደጋጋሚ በሚካሄደው ግጭት ላይ የአየር ጥቃት ሲፈፀም የአሁኑ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ ከአንድ አመት በፊት ጥቅምት ወር ላይ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ጮቢ ወረዳ ኦፉ ቀበሌ ልዩ ስሙ ቃሌ ተብሎ ሚጠራው ቦታ ላይ መንግስት በወሰደው የድሮን ጥቃት ከ68 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ አዲስ ስታንዳርድ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ከተወሰቡ ቀናት በኋላ ጥቅምት 30 ምዕራብ ወለጋ ዞን፣ መነ ሲቡ ወረዳ በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ቁጥጥር ስር ናት በተባለ መንዲ ከተማ ላይ በተወሰደ የአየር ጥቃት ከ20 በላይ ንፁሃን ሰዎች መሞታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ቢቢሲ መንግስት የወሰደው የአየር ጥቃት የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ተሸከርካሪ ላይ ያነጣጠረ ቢሆንም በአብዛኛው የሞቱት ንፁሃን ዜጎች ናቸው ሲል በወቅቱ ዘግቧል፡፡

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ግዜ ድረስ ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ ተፈፀመ ስለተባለው የአየር ጥቃት ከመንግስት በኩል የተገለፀ ነገር የለም፡፡ ነዋሪዎች በገለፁት መረጃ ላይ የሁለቱን ወረዳዎች ኃላፊዎች ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ ባለመሳካቱ አስታየታቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button