ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ በአፍሪካ ቀንድ ጎርፍ ያፈናቀላቸው ሰዎች ቁጥር ከሁለት ሚሊየን እንደሚበልጥ ተገለጸ፤ 300 የሚሆኑ ሰዎች ህይወት አልፏል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 21/2016 ዓ.ም፡- በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በተለይም በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ ጎርፍ ያፈናቀላቸው ሰዎች ቁጥር ከሁለት ሚሊየን እንደሚበልጥ ተገለጸ፤ የጎርፍ ባስከተለው አደጋ ህይወታቸው የላፈ ሰዎች ቁጥርም 300 እንደሚጠጋ ኤኤፍፒ የዜና አውታር ከእርዳታ ድርጅቶች እና ከሀገራቱ መንግስታት ያገኘውን መረጃ አጠናቅሮ አስታውቋል።

ከኤሊኖ ጋር በተገናኘ የተፈጠረው የአየር ንብረት ለውጥ የፈጠረው ነው በተባለው ጎርፍ የተከሰተው ቀጠናው በአርባ አመታት ውስጥ አይቶትየማያውቀው ድርቅ ተከትሎ መሆኑን ዘገባው ጠቁሟል።

በሶማሊያ ብቻ ከአንደ ሚሊየን ሰዎች በላይ በሀገሪቱ በተከሰተው ጎርፍ ሳቢያ መፈናቀላቸውን እና ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች ህይወት ማሳጣቱን የተባበሩት መንግስታት እና የሶማሊያ መንግስት መግለጻቸውን አስታውቋል። የጎርፍ አደጋ ሀገሪቱን ክፉኛ መጉዳቱን ተከትሎ የሀገሪቱ መንግስት አስቸኳይ ግዜ አደጋ ማወጁ ይታወሳል።

በተያዘው የታህሳስ ወር በሶማሊያ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ሄክታር የእርሻ ቦታን ጎርፍ ሊጠርገው ይችላል የሚል ፍራቻ መፈጠሩን ዘገባው አስቀምጧል።

በኬንያ በጎርፍ ሳቢያ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 136 መድረሱን እና 460ሺ ሰዎች መፈናቀላቸውንም ዘገባው አስታውቋል።

በኢትዮጵያም በጎርፍ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 600ሺ በላይ መሆናቸውን እና 57 ሰዎች መሞታቸውን ዘገባው ጠቁሟል።

በኢትዮጵያ በሶማሌ ክልል ኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱን እና 23 ሰዎች ህይወት ማሳጣቱን ዘገባው አመላክቷል። 772 ሰዎች በወረርሽኙ መያዛቸውንም ዘገባው ጠቁሟል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button