ዜናፖለቲካ

ዜና፡ መከላከያ በምዕራብ ሽዋ ዞን በሚንቀሳቀሰው የሸኔ ቡድን ላይ ወሰድኩት ባለው እርምጃ ዋና አመራሩን ገደልኩ ሲል አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10/2016 ዓ.ም፡- በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መንግስት “ሸኔ” ብሎ የሚጠራው ኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነስ) ታጣቂዎች ላይ በወሰደው እርምጃ የቡድኑ ከፍተኛ አመራር የሆነው ጃል ቦሩ አምቦን እና ሌሎች በርካታ የቡድኑ አባላትን መግደሉን አስታወቀ።

መከላከያ ሰራዊቱ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ፌስቡክ ገጹ ጥቅምት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ባሰፈረው መረጃ በአከባቢው የሚገኘው የመከላከያ የክፍለ ጦሩ የሠራዊት አባላት በምዕራብ ሽዋ ዞን በአቡና ግንደ በረት ወረዳ ፋጅና ጌርጌራ በተባሉ አካባቢዋች ላይ ጥቃት የሰነዘረውን የሸኔ ቡድንን ደምስሻለሁ ብሏል።

በተጨማሪም በርካታ የቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውን እና የተለያዩ የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎችን እና ተተኳሾችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ሻምበል እንግዳሸት መከተ የተባሉ የሰራዊቱ ከፍተኛ አመራር መናገራቸውን የመከላከያ የፌስቡክ ገጽ ላይ የሰፈረው መረጃ አካቷል።

በተመሳሳይ በጀልዱ ወረዳ በጩልቄ እና በሽኩቴ አካባቢዋች ላይ የሽብር ቡድኑ በሰነዘረው የማጥቃት ሙከራ እቅዱ ሳይሳካ ቀርቶ ስራዊታችን የሽብር ቡድኑን እኩይ ተግባር ቀድሞ በማክሸፍ እንዲመለስ ማድረጉን ሻምበል ከረሚላ ሙሃመድ መግለጻቸውን አስታውቋል።

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መንግስት “ሸኔ” ብሎ የሚጠራው ኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነስ) ታጣቂዎች ትላንት ጥቅምት 9/2016 ዓ.ም የኢስት ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራተኞች የሆኑ የቻይና ዜጎችን አግተው መውሰዳቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ታጣቂዎቹ ፊቼ ከተማን በቁጥጥራቸው ስር ለማዋል በማሰብ ጋረ ሹሂ በሚባል ቦታ ላይ ከመንግስት ጸጥታ ሀይሎች ጋር ረዘም ያለና ከፍተኛ ውጊያ ማድረጋቸውን እና በዚህም ሳቢያ የመንግስት አካል ባስተላለፈው ትዕዛዝ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትና ትምህርት ቤቶች ተዘግተው መዋላቸውን ነዋሪዎች ዋቢ በማድረግ በዘገባው አካተናል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button