ፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: ጠ/ሚኒስትሩ እና ርዕሰ መስተዳደሩ በመሳሪያ የተደገፈ ትግል ለሚያካሂዱ የአማራ ክልል ታጣቂዎች "መገዳደል ይብቃን" ሲሉ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5/2016 ዓ.ም፡- ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ በአማራ ክልል መሳሪያ አንግበው ትግል ላይ የሚገኙ ሃይሎች “ትጥቃቸውን ፈትተው በሰላማዊ መንገድ ኑ እና ታገሉ፣ መገዳደል ይብቃን” የሚል ጥሪ አቀረቡ።

ትላንት ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም በአባይ ወንዝ ላይ የተገነባውን ታላቁን ድልድይ መርቀው ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ “ጫካ ለሚገኙ ወንድሞቻችን” ሲሉ መሳሪያ አንግበር በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ባቀረቡት ጥሪ “ዛሬ አማራ መሪ አግኝቷል አረጋ ከበደን የመሰለ ታማኝ፣ ትጉህ መሪ አግኝቷል” ሲሉ በማወደስ “ለአማራ መብት የሚታገል ግለሰብም ይሁን ቡድን ከአረጋ አመራር ስር ሁኖ ክልሉን እና ህዝቡን መጥቀም ስለሚችል መገዳደል ይብቃን” ሲሉ አሳስበዋል።

“ኑ ወደ ክልላችሁ ተመለሱ ክልላችሁን ሰላም ጠብቁ…. መገዳደል ይብቃን” ብለዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ለጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ (ዶ/ር) ምሥጋና ባቀረቡበት መልዕክታቸው “በጫካ ለምትገኙ ወንድሞቻችን” ሲሉ በመጥራት “በእውነት ከክልላችን ሕዝብ ጥቅም እና ክብር ውጭ ሌላ ስውር አጀንዳ ከሌላችሁ በስተቀር ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) ባቀረቡላችሁ ጥሪ መሠረት ችግሮቻችንን በውይይት እና በድርድር እንድንፈታና ሕዝባችንም እፎይታ እንዲያገኝ በድጋሜ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ” ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ለባሕር ዳር እና አካባቢዋ ነዋሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት ደግሞ “በፀረ ሰላም ኀይሎች የነበረባችሁን ጫና ከምንም ሳትቆጥሩ በምረቃ ቦታው በመገኘት እና እንግዶችን በመቀበል ላሳያችሁት ፍቅር እና አክብሮት በራሴ እና በክልላችን መንግሥት ስም ከፍ ያለ ምሥጋናየን አቀርባለሁ” ብለዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button