ዜናቢዝነስ

ዜና፡ የደቡብ ወሎ ዞን የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር በኦፓል ማዕድን ልማት ላይ ከፍተኛ እንቅፋት መፍጠሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29/2016 ዓ.ም፡- የደቡብ ወሎ ዞን በማዕድን ሐብት ልማት ለበርካታ ባለሐብቶች ፈቃድ ቢሰጥም የፀጥታ ችግሩ ወደ ሥራ ለማስገባት ተጽዕኖ ማሳደሩን የዞኑ ማዕድን ሐብት ልማት መምሪያ አስታወቀ። የጸጥታ ችግር በተስተዋለበት የበጀት አመቱ መጀመሪያ ወራት ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ኦፓል ለውጭ ገበያ መቅረቡን ከደቡብ ወሎ ዞን ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

በ2016 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ አመት 6 ሺ 532 ኪሎ ግራም ኦፓል ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን መረጃው ጠቁሟል። በሩብ አመቱ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በዘርፉ የሚፈለገውን ያህል መሥራት አለመቻሉን የመምሪያ ኃላፊው አቶ አህመድ አበባው መናገራቸውን አካቷል።  ከጸጥታ ችግር በተጨማሪ በዞኑ ለማእድን ልማት የሚሆነውን መሬት ከሦስተኛ ወገን ነፃ አለማድረግ፣ የብድር አቅርቦት አለመመቻቸት፣ የኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት አለመኖር ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውንም ሃላሂው መግለጻቸውን የዞኑ ኮሙዩኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።

ደቡብ ወሎ የኦፓል፣ የድንጋይ ከሰል፣ የኦይል ሸል፣ የነዳጅ፣ የአምበር፣ የጃስፐር፣ የአጌት፣ የኦኒክስ፣ የቶርማሊን፣ የኳርቲዝ፣ የጅፕሰምና የሌሎች ከ30 በላይ የሚሆኑ ማዕድናት ባለቤት ስለመሆኑ ተረጋግጧል ሲሉ የዞኑ ማዕድን ሐብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ አበባው ተናግረዋል ያለው መረጃው እነዚህንም የኢነርጂ፣ የጌጣጌጥና የኢንዱስትሪ ማዕድናት በሩብ ዓመቱ የመለየት ሥራ ተከናውኗል ማለታቸውን አስታውቋል።

ለ84 ባለሐብቶች አነስተኛ የማዕድን ሥራ ፈቃድ መሰጠቱን እና ከነዚህ ውስጥ 47 የሚሆኑት በሥራ ሂደት ላይ የሚገኙ ሲሆን 19 በሚሆኑት ላይ ደግሞ በተለያዩ ጥፋቶች ምክንያት ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ መደረጉን መምሪያ ኃላፊው መናገራቸውንም ጠቁሟል።

42 ባህላዊ የማዕድን ሥራ ፈቃድ መሰጠቱን እና በዚህም ለ428 ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ከ694ሺ ብር በላይ ገቢ መገኘቱን መረጃው አካቷል፡፡ አስ  

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button