ዜናቢዝነስ

ዜና፡ የኢትዮጵያን የሎጂስቲክ ስርአት ለማዘመን የሚያግዝ ማስተር ፕላን በአውሮፓ ህብረት ድጋፍ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1/2016 .ም፡ በኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ስርዓቱን የሚያዘመን እና አፈጻጸሙን ለማሳደግ ያለመ የሎጂስቲክስ ረቂቅ ማስተር ፕላን በአውሮፓ ሕብረት ድጋፍ በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ተጠቆመ።

ማስተር ፕላኑ ለመጪዎቹ 30 ዓመታት የሚኖረውን የሎጂስቲክስ ጉዞ በአግባቡ እንዲጠቁም ተደርጎ በመዘጋጀት ላይ ነው ተብሏል።

በአውሮፓ ሕብረት የገንዘብ ድጋፍ ‘ዲቲ ግሎባል’ በተሰኘ አማካሪ ድርጅት በኩል የተጠናው የሎጂስቲክስ ማስተር ፕላን የመጀመሪያ ምዕራፍ ረቂቅ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መካሄዱን ኢዜአ ዘግቧል።

ሎጂስቲክስ ለሁሉም ኢኮኖሚ ዘርፎች የደም ስር በመሆኑ የዘርፉን ዕቅድ በየጊዜው መከለስ እና ማሻሻል ይጠይቃል ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ ገልጸዋል ያለው ዘገባው መንግሥት ጠንካራ የሎጂስቲክስ ስርዓት ለመገንባት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ቀርጾ ወደስራ ገብቷል ማለታቸውን አመላክቷል።

በስትራቴጂው ከተቀመጡ መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል የሎጂስቲክስ ማስተር ፕላን ማዘጋጀት አንዱ በመሆኑ ለመጪዎቹ 30 ዓመታት የሚኖረውን የሎጂስቲክስ ጉዞ በአግባቡ የሚጠቁም ረቂቅ ማስተር ፕላን መዘጋጀቱን ገልጸዋል ብሏል።

ማስተር ፕላኑ የሀገሪቷን ሎጂስቲክስ አፈጻጸም በማጎልበት የብዝሀ ኢኮኖሚ ግንባታን የሚያግዝ፣ የዘርፉን ክፍተቶች በመለየትና የቀጣይ መዳረሻን የሚያመላክት ነው ማለታቸውንም አካቷል።

ከማስተር ፕላኑ ጥቁምታዎች መካከል አማራጭ ወደብ መጠቀም አንዱ የመፍትሔ ሃሳብ እንደሆነ ጠቅሰው፣ በቅርቡ የተደረገው የኢትዮ-ሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነትም ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ማለታቸውንም አስታውቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አብዱልበር ሸምሱ፥ ረቂቅ ማስተርፕላኑ በተቋም ደረጃ መገምገሙን ገልጸው፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገበት መሆኑን ተናግረዋል።

ማስተርፕላኑ የዘርፉን ማነቆዎች ለይቶ መፍትሄ ለማስቀመጥ፣ የሎጂስቲክስ ስርዓቱን በዲጂታላይዜሸን ለማዘመን እና ጸጋዎችን በመለየት በተቀናጀ አግባብ ለይቶ ለመጠቀም እንደሚረዳ ገልጸዋል።

የዲቲ ግሎባል ድርጅት ተወካይ ዶክተር ማርክ ፔርሰን፥ ሎጂስቲክስን ማዘመን ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል። ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ማስተር ፕላን ማዘጋጀቷ፤ የዘርፉን ችግሮች በመለየት ለመፍታት እንደሚያስችላት ነው የተናገሩት።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button