ፖለቲካ

ዜና: በነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ላይ የነበረው ከፍተኝ የዕዳ ጫና ወደ 89 ቢሊየን ዝቅ ማለቱ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1/2016 ዓ.ም፡- መንግስት የነዳጅ ሪፎርም ተጠናክሮ መቀጠሉ በነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ላይ የነበረውን ከፍተኝ የዕዳ ጫና ዝቅ እንዲል አድርጊያለሁ ሲል ገለጸ።

ለነዳጅ ሲደረግ የነበረው ድጎማ ቀስ በቀስ መወገዱ ለጫናው መቀነስ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን አመላክቷል።

በአሁኑ ወቅት በነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ላይ የነበረው ከፍተኝ የዕዳ ጫና ወደ 89 ቢሊየን ዝቅ ማለቱ የጠቆመው መንግስት በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም ጨናው 124 ቢሊየን ደርሶ እንደነበር አስታውሷል።

የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ከ20 ዓመታት በፊት የተቋቋመ ሲሆን የአለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ በሀገሪቱ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመቋቋም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ተገልጿል።

ብሔራዊ የነዳጅ ሪፎርም እስቲሪንግ ኮሚቴ ባለፉት አስር ወራት የነበረውን የነዳጅ አፈጻጸም በመገምገም የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ከንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ብሔራዊ ኮሚቴው በንግድና ቀጣናዊ ትስሰር ሚኒስትሩ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ሰብሳቢነትና በዶ/ር ዓለሙ ስሜ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትር ም/ሰብሳብነት ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ፣የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን፣ የኢት/የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እና ኢትዮ ቴሌኮም በአባልነት ይገኙበታል።

ባለፉት አስር ወራት በታቀደው መሰረት ስራዎች መሰራታቸውን የተመለከተው ኮሚቴው በዲጂታል የነዳጅ ግብይት የሚካሄደውን መረጃ በማዕከል ለማደራጀት እየተጠና ያለው ሲስተም ልማት መጠናቀቅ ደረጃ ላይ መድረሱን፣ ነዳጅ ስርጭትን ከግዥ ትዕዛዝ ጀምሮ ከወደብ ከጫነ በኋላ ማደያ እስኪራገፍ ድረስ ያለውና ከተራገፈ በኋላ የነዳጅ ስርጭቱ በድጅታል መፈፀሙን ኦዲት ለማድረግ የሚያስችል ሲስተም ጥናት ተጠናቆ ወደ ሙከራ ትግበራ መግባት መቻሉና እስካሁን የታለመለት የነዳጅ ድጎማን ያለአግባብ የወሰዱ ተሽከርካሪዎች ላይ ኦዲት በማድረግ እርምጃ መውሰድ መጀመሩ በጠንካራ አፈጻጸም ገምግሟል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

አዳዲስ የነዳጅ ኩባንያ እና የነዳጅ ማደያ መገንባት እንዲቆም ቀደም ሲል በተወሰነው ውሳኔ መሰረት አፈጻጸሙ ክትትል እንዲደረግበት፣ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ምዝገባ አዲስ በሚለማው የተሽከርካሪ መረጃ ማዕከል እንዲደራጅ ሲል ኮሚቴው ውሳኔውን ማሳለፉንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

በተያያዘ ዜና መንግስት ከስምንት ወራት በኋላ በቤንዚን የችርቻሮ ዋጋ ላይ ጭማሪ መደረጉን አስታውቋል።

መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም የቤንዚን የችርቻሮ መሸጫ በሊትር 77 ብር ከ65 ሳንቲም የነበረ ሲሆን ከዛሬ ከግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም በኋላ የአንድ ሊትር ቤንዚን መሸጫ ዋጋ 78 ብር ከ67 ሳንቲም መሆኑን ጠቁሟል።

ከግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ከቤንዚል ውጪ ባሉ የነዳጅ ምርቶች ዋጋ ባለበት እንደሚቀጥል መወሰኑን አመላክቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button