ዜናማህበራዊ ጉዳይ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ኢትዮጵያና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጎርፍ አደጋ ለተጎዱ 1.5 ሚሊዮን ዜጎች አፋጣኝ ድጋፍ እንዲደረግ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 20/ 2016 ዓ/ም፦ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ባጋጠመ የጎርፍ አደጋ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን እና 600 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የኢትዮጵያ መንግስት በጋራ ባውጡት መግልጫ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽፈራው ተክለ ማርያምና በኢትዮጵያ የተመድ ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ራሚዝ አላክባሮቭ የጎረፍ አደጋው ያደረስውን ጉዳት ለመገምገም እና የእርዳታ ጥረቶችን ለማሳደግ የሚረዱ አማራጮችን ለማሰስ በስፈራዎቹ በመገኘት ከህዳር 14 እስክ 16 የሶስት ቀን ጉብኝት አደረገዋል።

የጎርፍ አደጋው በሰባት ክልሎች በ23 ዞኖችና በ85 ወረዳዎች የተከሰተ ሲሆን ከፍተኛ ውድመት ማሰከተሉ፣ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ማድርሱ፣ ነዋሪዎችን ከቀያቸው ማፈናቀሉ፣ የሰብል፣ የእንስሳትና መሰረተ ልማቶችን ማወደሙ ተገልጿል። “ቤቶች፣ ሱቆች፣ ትምህርት ቤቶች እና የእርሻ መሬቶች በውሃ ተውጠዋል። በተጨማሪም የጤና ችግሮች እየጨመሩ በመምጣታቸው የኮሌራ፣ የወባ እና የመሳሰሉ በሽታዎች እንዲባባሱ አድርጓል” ሲል መግለጫው ገልጿል።

በጎርፍ አደጋው ከተጎዱት 80 በመቶውን የሚይዘው ሶማሊ ክልል፤ ሸበሌ፣ አፍዴር፣ ሊበን እና ዳዋ ዞኖች ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል ነው የተባለው። “በአንዳንድ አካባቢዎች፣ ማህበረሰቦቹ በዓመታት ወስጥ ከታዩት የጎርፍ አደጋዎች የአሁኑ የከፋ እንደሆነ ገልጸዋል” ብሏል መግለጫው።

በጋራ መግለጫው በኢትዮጵያ መንግስት እና በአጋር ግብረሰናይ ደርጅቶች ለተጎጂዎች እየተሰጠ ያለው ዘርፈ ብዙ ህይወት የማዳን ዕርዳታ “በቂ አለመሆኑ” ተመላክቷል። በሶማሊ ክልል ከ 1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተጎጂ የሆኑ ሲሆን 500 ሺህ ነዋሪዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ክዚህ ውስጥ ዕርዳታ ያገኙት 10 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው ተብሏል።

በመከናወን ላይ ካለው ህይወት የማዳን ተግባር በተጨማሪ መንግስት የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሄሊኮፕተሮችን እና ጀልባዎችን ለህይወት አድን ስራ እና አስቸጋሪ ወደሆኑ አካባቢዎች እርዳታዎችን ለማጓጓዝ ቢያሰማራም አሁንም የጎላ ክፍተቶች መኖራቸውን መግለጫው በአጽንኦት ገልጿል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አታለለ አቡሀይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት መንግሥት በጎርፍ፣ በግጭትና በድርቅ ለተጎዱ 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች በሁለት ዙር 7 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ርዳታ ማድረሱን አስታውቀዋል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የጋራ መግለጫው ተጎጂዎችን ለመርዳት ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ማጋጠሙንና በጎርፍ የተጠቁ አከባቢዎች ዕርዳታ ተደራሽ ለማድርግ ምቹ አለመሆናቸው ትልቅ ፈተና እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን “ተጨማሪ ድጋፎችን እና የሎጂስቲክስ አቅምን በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማሰባሰብ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ” ጥሪ አቅርቧል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button