ዜናቢዝነስ

ዜና፡ የአበባ እርሻ የሚያስከትለው ጉዳት በገለልተኛ አካል ተጠንቶ እንዲቀርብ ፓርላማው ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 24/2016 ዓ.ም፡- ግብርና ሚኒስቴር የአበባ እርሻ ልማት በአካባቢ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በገለልተኛ ቡድን አስጠንቶ እንዲያቀርብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በግብርና ሚኒስቴር የአበባ እርሻ ልማት ምርታማነትና የአካባቢ አያያዝ ሥርዓት ውጤታማነትን በተመለከተ የ2014/2015 በጀት ዓመት ክዋኔ ኦዲት ግኝት ላይ ውይይት ማድረጉን ኢፕድ ዘግቧል።

የአበባ ልማት በሀገሪቱ ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ዘርፍ ቢሆንም የራሱ የአሠራር መመሪያ የለውም ሲሉ የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ አራሬ ሞሲሳ ገልጸዋል ያለው ዘገባው ከአበባ እርሻ ልማት ጋር ተያይዞ በአካባቢ ላይ የደረሰው ጉዳት በገለልተኛ አካላት ማስጠናት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ይህ መሆኑ ተጓዳኝ ችግሮችን ማወቅና የመፍትሄ ርምጃ ለመውሰድ ያግዛል ማለታቸውን አስታውቋል።

የአበባ ልማት ያስከተለው ጉዳት በገለልተኛ ቡድን ተጠንቶ ሪፖርቱ እንዲደርሰን እንፈልጋለን ያሉት ምክትል ሰብሳቢዋ፤ ተቋሙ የድርጊት መርሀ ግብሩንም እስከ ህዳር 30 ለቋሚ ኮሚቴውና ለሚመለከታቸው አካላት መላክ እንዳለበት ማሳሰባቸውንም አመላክቷል።

የአበባ ልማት ሥራው የዜጎችን ደህንነት በጠበቀ መልኩ እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት በደንብ በማጠናከር የክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የተጠያቂነት ሥርዓት ሊኖር እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው ማሳሰቡንም አካቷል።

ለአበባ ልማቱ ፖሊሲና ደንብ ሳይዘጋጅበት እየተሠራ በመሆኑ ዘርፉን ለመምራት የሚያስችል ደንብና አሠራር መዘርጋት ይገባል ሲሉ ምክትል ሰብሳቢዋ አሳስበዋል ያለው ዘገባው በዘርፉ እየተዘጋጀ ያለው መመሪያ ጸድቆ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ለገንዘብ ሚኒስቴር፤ ለፌዴራል ኦዲት መስሪያ ቤት፤ ለምክር ቤቱ የግብርና ጉዳዮችና ለመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ እንዲቀርብ መጠየቃቸውን አስታውቋል።

የአበባ አልሚ ድርጅቶች የሚጠቀሟቸው ግብአቶችና ኬሚካሎች የሚያመጡትን ተጽዕኖ ለመከላከልና ተገቢ የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ሁኔታዎች እንዲኖሩ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛል ሲሉ በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) መግለጻቸውን ዘገባው አካቷል። በቋሚ ኮሚቴው በተሰጡ አስተያየቶች መሰረት ከሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን በድርጊት መርሀ ግብሩና በኦዲት ግኝቱ መሰረት ለማስተካከል እንደሚሠሩ መግለጻቸውንም አመላክቷል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button