ማህበራዊ ጉዳይዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በግብፅ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ለእንግልት እና ለዘፈቀደ እስር እየተዳረጉ መሆኑን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10/ 2017 ዓ/ም፦ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ውጥረት ተባብሶ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት በግብፅ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ለዘፈቀደ እስርና እንግልት እየተዳረጉ መሆኑን ገለጹ።

በግብፅ የሚገኙ የማህበረሰብ መሪዎች እና ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለፁት እነዚህ ስደተኞቹ የገንዘብ ብዝበዛ፣ እንግልት፣ የዘፈቀደ እስራት እና ጥቃቶችን ጨምሮ ለበርካታ ችግሮች እየተዳረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በ2011ዓ.ም በግብጽ ጥገኝነት የጠየቁ እና ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ በግብጽ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ መሪ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ከህግ አግባብ ውጭ እየታሰሩ እንደሚገኙ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

“ከታሰሩት ውስጥ አብዛኞቹ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን መታወቂያ ካርድ አላቸው” ሲሉ የገለጹት በግብጽ የማህበረሰብ መሪው አክለውም አንዳንዶቹ የአገልግሎት ጊዜው ያለፈበት መታወቅያ የያዙ ነገር ግን በእድሳት ሂደት ላይ የሚገኙ ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ ህጋዊ ናቸው” ብለዋል። 

በተጨማሪም “በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ስደተኛ ተብለው እውቅና የተሰጣቸው እና እንደ ነጭ ካርድ፣ ቢጫ ካርድ እና የጥገኝነት ጠያቂዎች የመመዝገቢያ ካርድ ያሉ የተለያዩ መታወቂያ ካርዶችን የያዙ ስደተኞች ሳይቀሩ በግብፅ ለተለያዩ ፈተናዎችን መዳረጋቸው ቀጥሏል” ብለዋል።

እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች እንዲፈታ በኢትዮጵያ ማህበረሰብ ህብረት እና በኦሮሞ ኢልደርስ ህብረት በኩል ለኮሚሽኑ በማሳወቅ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።

“የማህበረሰብ አባላት መታሰራቸውን ስናውቅ፣ ወዲያውኑ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በኢሜይል አሳውቀናል” ሲሉ በግብጽ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ መሪው አክለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

“ይህንን ግንኙነት ተከትሎ ኮሚሽኑ ከማህበረሰቡ መሪዎች ጋር አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ ችግሮቹን ለመፍታት ቃል ገብቷል” ብለዋል። ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ውጤታማ መፍትሄዎች አለመተግበራቸውን ጠቁመዋል።

በ2006 ዓ.ም. ከወንድማቸው መሀመድ አሊ ጋር ወደ ግብፅ የተሰደዱት የ36 አመቱ አቶ ሱለይማን አሊ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት በጥገኝነት ጠያቂነት ለመመዝገብ ቡሞክሩም እስካሁን ድረስ አለመመዝገባቸው ተናግረዋል።

አቶ ሱለይማን አክለውም ወንድማቸው በጥር ወር 2016 ዓ.ም. የወንበዴዎች እና የፖሊስ ጥቃት መፈጸምን ተከትሎ ካይሮ በሚገኘው ባሳቲ እስር ቤት ውስጥ ታስረው እንደነበረ ተናግረዋል። በወቅቱ ወንድማቸው ለፖሊስ ገንዘብ ቢከፍሉም ከመለቀቃቸው በፊት ለሁለት ወራት ያህል በእስር ላይ እንዲቆዩ ተደርገዋል ብለዋል። 

በተጨማሪም “ከወንድማቸው ጋራ አብረው በካይሮ ታስረው የነበሩ አንዳንድ ስደተኞች አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ” ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ለእሳቸው፣ ለወንድማቸው እና ለሌሎች ስደተኞች ነጭ ወረቀት ቢሰጣቸውም፣ “ጠቀሜታ የጎደለው ነው በሚል የግብጽ መንግስት እውቅና ሊሰጠው አልቻለም” ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል።

“ከዚህ ቀደም በግብፅ ውስጥ ከባድ ችግሮች ሲያጋጥሙን እኛ (ኢትዮጵያውያን ስደተኞች) ሱዳን ለመጠለል እናስብ ነበር” ሲሉ ገልጸው “ሱዳን በአሁኑ ወቅት በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የምትገኝ በመሆኑ ይህን እንደ አማራጭ መጠቀም አይሆንም” ሲሉ ተናግረዋል።

በግብፅ የሚኖሩ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ መሪ እና ስደተኞች በበኩላቸው በግብፅ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በጅምላ ማሰር የተጀመረው በሚያዝያ ወር 2015ዓ.ም. መሆኑን አስረድተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌትን ተከትሎ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል እየጨመረ ከመጣው አለመግባባት ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ የሚፈጸሙ እንደ የገንዘብ ብዝበዛ፣ እንግልት፣ የዘፈቀደ እስራትና የመሳሰሉ እርምጃዎች ተባብሰው መቀጠላቸውን በአጽንኦት ገልጸዋል።

በግብፅ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በዚህ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት መሃል ሆነው በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸው ችግሮች በመባባስ ላይ ይገኛሉ።

በሰኔ 2015 ዓ.ም በግብፅ በብዛት ተነባቢ የሆነው አል-አህራም ጋዜጣ እንደዘገበው በወቅቱ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በካይሮ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ቢሮ ደጃፍ በመሰባሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመጣው የ “ግብፃውያን የውጭ ዜጋ ጥላቻ ከወለደው ጥቃት” ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

በዘገባው መሰረት በወቅቱ ስደተኞቹ የማህበረሰባቸው አባላት በግብፅ በርካታ ጥቃቶች እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።

በግብፅ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እነዚህ ተግዳሮቶች አሁንም ድረስ መቀጠላቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በግብፅ የሚኖሩ ሌላ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ስደተኛ እና የማህበረሰብ መሪ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ያለ ምንም ምክንያት በጅምላ የመቃወም ተግባር በ2016 ዓ.ም ማየሉን ተናግረዋል።

“ከየትኛውም የፖለቲካ ቡድን ጋር ግንኙነት የለንም፤ እኛ በቀላሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ሰነድ ስር የተካተትን ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ነን” ሲሉ የገለጹት የማህበረሰብ መሪው ሆኖም በሁለቱ አገራት መካከል ባለው አለመግባባት የተነሳ ትንኮሳዎች፣ የዘፈቀደ እስራት እና የጥቃት ሰለባ ሆነናል ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

የማህበረሰብ መሪው በተጨማሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት በግብፅ ውስጥ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የትግሬ እና ሀዲያን ጨምሮ 12 የሚደርሱ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ አባላት እንደሚገኙ ጠቅሰው ሁሉም ለችግሮች ሰለባ ናቸው ብለዋል።

“ኢትዮጵያውን ስደተኞቹ በተለይ ባሳቲ እና ዳሩሳላም በተሰኙ እስር ቤቶች እንዲሁም በካይሮ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ሌሎች እስር ቤቶች ለእስራት ይዳረጋሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

በግብፅ የማህበረሰብ መሪ እንደመሆናቸው፣ በየእለቱ አራት ወይም አምስት የሚደርሱ ስደተኞች እስር ሪፖርት እንደሚደርሳቸው ገልጸዋል።

በተጨማሪ “ለእስረኞቹ ምግብ ለማቅረብ ስትሄድ ፖሊሶች ገንዘብ ይጠይቃሉ” ሲሉ አክለዋል።

የማህበረሰቡ መሪ አክለው እንደገለጹት፤ ከእሳቸው የማህበረሰበ አባላት ቢያንስ 100 የሚሆኑ ገለሰቦች ታሰረዋል።

አክለውም “እንደ ማህበረሰብ መሪ የነዚህን አንድ መቶ እስረኞች ሁኔታ በተመለከተ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን አሳውቂያለሁ  ነገር ግን ምንም ምላሽ አላገኘሁም” ብለዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button