ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና: አዲስ አበባ በፈረንጆቹ 2035 በአፍሪካ ከሚገኙ ቁልፍ ከተሞች ተርታ እንደምትሰለፍ ኢኮኖሚስት ያወጣው ሪፖርት አመላከተ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6/2017 ዓ.ም፡- እ.ኤ.አ በ2035 አዲስ አበባ በአፍሪካ ከሚገኙ  ቁልፍ ከተሞች ተርታ ትሰለፋለች ሲል ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት (Economist Intelligence Unit) አዲስ ባወጣው የትንበያ ሪፖርት አስታወቀ።

ሪፖርቱ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ የኮንጎዋ ብራዛቪል፣ የታንዛንያዋ ዳሬሰላም እና የአንጎላዋ ሉዋንዳ በቀጣይ በአፍሪካ ከሚገኙ ቁልፍ ከተሞች ተርታ እንደሚመደቡ አመላክቷል።

ተቋሙ “የአፍሪካ ከተሞች በ2035” በሚል ርዕስ የቀረበው ሪፖርት እንዳመላከተው እንደ ካይሮ፣ ሌጎስ እና ጆሃንስበርግ ያሉ የአፍሪካ ግዙፍ ከተሞች የኢኮኖሚ የበላይነታቸውን አስጠብቀው ይቀጥላሉ ያለ ሲሆን፣ እንደ አዲስ አበባ ያሉ መካከለኛ ከተሞች ደግሞ በከፍተኛ ፍጥነት የዕድገት ደረጃ ሊያገኙ እንደሚችሉ ጠቁሟል።

ተቋሙ ለዚህም በምክንያትነት ያስቀመጠው እንደ መሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ የከተሞች መስፋፋት እና በአቅራቢያቸው የሚገኙ ከተሞች ማደግ እና ሌሎች ተያያዥ መሰል ምክንያቶች መሆናቸውን አመላክቷል።

አዲስ አበባ ከአፍሪካ ከተሞች አስደናቂ  የኢኮኖሚ ዕድገት ባለቤት ሆና እውቅና ያገኘች ሲሆን እ.ኤ.አ እስከ 2035 ድረስ በአመት ባለሁለት አሃዝ እና ከዚያ በላይ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገትን እንደምታስመዘግብ ትንበያው ጠቁሟል።

በአንፃሩ እንደ ናይሮቢ እና አቡጃ ያሉ ከተሞች በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ከ6 በመቶ እስከ 8 በመቶ የእድገት ምጣኔ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል ብሏል።

ሪፖርቱ በተጨማሪ በአፍሪካ ከገጠር ወደ ከተማ የሚኖረው ፍልሰት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በተለይም በከተሞች ላይ ፈጣን የህዝብ ቁጥር እድገት እየተመዘገበ መሆኑን አመልክቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

እ.ኤ አ በ2023 በአፍሪካ 650 ሚሊዮን ገደማ የነበረው የከተማ ህዝብ ቁጥር እ.ኤ.አ በ2035 ወደ አንድ ቢሊየን ያድጋል የተባለ ሲሆን፣ በዚህም እ.ኤ.አ በ2035 ከ50 በመቶ በላይ አፍሪካውያን በከተሞች እንደሚኖሩ ሪፖርቱ ጠቁሟል።

ሆኖም ይህ ፈጣን የከተሜነት መስፋፋት በከተሞች አከባቢ ከፍተኛ መጨናነቅን፣ መደበኛ ያልሆኑ ሰፈራዎች መስፋፋትን እና ከፍተኛ ስራ አጥነትን እና የአገልግሎት እጥረትን ጨምሮ የተለያዩ ፈተናዎችን ሊያመጣ ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።

ይህ የኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት ዘገባ የወጣው ከነሐሴ 29 እስከ ጳጉሜ 1/2016 ዓ.ም.በአዲስ አበባ የተካሄደው የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም ከተጠናቀቀ ከሳምንት በኋላ ነው።

ፎረሙ ከ47 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ተወካዮችን፣ የከተማ ፕላነሮችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችን፣ ምሁራንን እና የማህበረሰብ መሪዎችን ያሳተፈ ነበር።

ለሶስት ቀናት የተካሄደው ፎረሙ የአፍሪካ አጀንዳ 2063 የትራንስፎርሜሽን እቅድ አካል ሆኖ በዘላቂ የከተሞች እድገት ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሄለን ደበበ በበኩላቸው ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን እንደገለጹት: በአፍሪካ የከተሞች መስፋፋት በፍጥነት እየጨመረ ቢመጣም ይህን እድገት ለመደገፍ የሚያስችሉ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች እንደሚያስፈልጉ አመልክተዋል።

ዘገባዎች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ በግምት 23 በመቶ የሚሆነው ህዝብ በከተሞች ውስጥ ይኖራል። የመንግስታቱ ድርጅት የስነ ህዝብ ድርጅት (UNFPA) ጥናት እንደሚያመለክተው እ.ኤ.አ በ2021 በኢትዮጵያ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው የፍልሰት መጠን 32.2 በመቶ ደርሷል ብሏል::

ይህ የስነ ሕዝብ አወቃቀር ለውጥ በአብዛኛው  በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች እንዲሁም እየጨመረ በመጣው የወጣቶች ስራ አጥነት ችግር ምክንያት የተከሰተ መሆኑ ተመላክቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button