ማህበራዊ ጉዳይዜናፖለቲካ

ዜና፡ በአማራ ክልል የተከሰተው የጸጥታ ችግር የድርቅ ተጎጅዎችን ለመደገፍ የሚሠራውን ሥራ አስቸጋሪ አድርጎታል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 11/2016 ዓ.ም፡- በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር የድርቅ ተጎጅዎችን ለመደገፍ የሚሠራውን ሥራ አስቸጋሪ አድርጎታል ሲሉ የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ማስታወቁን አሚኮ ዘግቧል።

ሁሉም የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ነጻ እንቅስቃሴን መፍቀድ እና ለተቸገሩት መድረስ ያስፈልጋል ሲሉ ኮሚሽነር ተስፋው ባታብል መናገራቸውንም ዘገባው አካቷል።

በክልሉ በ2015/16 የምርት ዘመን በተከሰተው ድርቅ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለችግር መጋለጡን በእንስሳት ላይም ጉዳት ማድረሱን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል ያለው ዘገባው በክልሉ ዘጠኝ ዞኖች፣ አርባ ሁለት ወረዳዎች እና በ425 ቀበሌዎች ላይ ድርቅ መከሰቱን እና በተለይ ግን በተከዜ ተፋሰስ ችግሩ እንደሚጎላ መግለጻቸውን አስታውቋል።

በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት የተከሰቱ ተደራራቢ ችግሮች ማኅበረሰቡን ለችግር እንዲጋለጥ አድርገውታል ያለው ዘገባው በተለይም ደግሞ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተከሰተው ጦርነት 11 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሕዝብ ተፈናቅሎ እንደነበር የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን መረጃን ዋቢ በማድረግ አመላክቷል።

በሰሜን ጎንደር ዞን ጃናሞራ፣ በየዳ እና ጠለምት ወረዳዎች፣ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰሃላ፣ ዝቋላ እና አበርገሌ ወረዳዎች፣ በማዕከላዊ ጎንደር ምዕራብ እና ምሥራቅ በለሳ እና ኪንፋንዝ በገላ ወረዳዎች፣ በደቡብ ጎንደር መቀጠዋ ወረዳ፣ በሰሜን ወሎ ራያ፣ ሀብሩ እና በከፊል ጉባላፍቶ ወረዳዎች፣ በደቡብ ወሎ ደግሞ አርጎባ እና ተንታ ወረዳዎች የከፋ ችግር እንዳለባቸው ጠቁሟል።

በአጠቃላይ በክልሉ ከ1 ሚሊዮን 846 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለችግር መጋለጫቸውን የጠቆመው ዘገባው ሕጻናት፣ እናቶች እና አረጋውያን ደግሞ ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውን፣ እንስሳት ላይም ጉዳት መድረሱን ኮሚሽነሩ መናገራቸውን አካቷል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button