ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ የነዳጅ ድጎማን በህገወጥ መንገድ ሲጠቀሙ የነበሩ 40 ሺህ ተሽከርካሪዎች ከስርአቱ እንዲወጡ ተደርጓል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 20/ 2016 ዓ/ም፦ የታለመለት የነዳጅ ድጎማን ላልተገባ ዓላማ ሲጠቀሙ የነበሩ 40 ሺህ ተሽከርካሪዎች ከድጎማ ስርዓቱ እንዲወጡና ዕዳ እንዲከፍሉ መደረጉን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጹ።

ሚኒስትሯ ይህን ያሉት የመንግሥት የ2016 የመጀመሪያ የሩብ ዓመት አፈጻጸም በተገመገመበት ወቅት ሲሆን የግምገማው ተሳታፊዎች “ድጎማው ሃብታሞችን እንጂ ድሃውን ማህበረሰብ በሚፈለገው ልክ አልጠቀመም” ሲሉ ተችተዋል። መንግሥት የችግሩን ጥልቀት ምን ያህል ያውቀዋል፤ ምንስ እርምጃ ወስዷል ሲሉም ጠይቀዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም በሰጡት ምላሽ፤ መንግስት የድጎማ ስርዓቱን ሲዘረጋ አቅም የሌላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በብዙሃን ትራንስፖርት ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም ስርዓቱ መተግበር ከጀመረ ወዲህ 23 ቢሊዮን ብር በብዙሃን ትራንስፖርት ለተሰማሩ አካላት  በድጎማው አማካይነት መሰጠቱን አስረድተዋል።

የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ስርዓት  ሌላኛው ዓላማ ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ታሪፍ የተሻለ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ ሆኖም አፈጻጸሙ ላይ ችግር መስተዋሉን ገልጸዋል።

ለህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የተሰጣቸውን የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉና በህገወጥ መንገድ ሲጠቀሙ የነበሩ 40 ሺህ ተሽከርካሪዎች ከድጎማ ስረአቱ እንዲወጡ መደረጉን ገልጸዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ከዚህም ባለፈ መንግስት ለህዝብ ተጠቃሚነት እንዲሰሩ ሲሰጣቸው የነበረውን የድጎማ ገንዘብ በዕዳ መልኩ መልሰው እንዲከፍሉ መደረጉን አስረድተዋል።

ዶክተር ፍጹም አክለውም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ነዳጅን በህገወጥ መንገድ የሚያዘዋውሩና በኮንትሮባንድ ወደ ውጭ የሚልኩ አካላት ላይ በጥብቅ ክትትል እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም ነዳጅ ከመነሻ ወደብ እስከ ተጠቃሚው የሚደርስበት አጠቃላይ ሰንሰለት ላይ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቁጥጥር ለማድረግ የዲጂታል ስርዓት ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው ከወደብ የተጫነውን የነዳጅ መጠን፣ የተጓዘበትንና ያረፈበትን መዳረሻ፣ የተራገፈበትን ማደያ፣ ከተራገፈው ውስጥ የተሸጠውን የነዳጅ መጠን እንዲሁም በዲፖ ውስጥ ያለውን ቀሪ የነዳጅ መጠን በአግባቡ መከታተል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ የታለመለት የነዳጅ ተጠቃሚዎች ህብረተሰቡን በተቀመጠው ታሪፍ እንዲያገለግሉም የኤሌክትሮኒክስ ትኬት ለመጀመር መታሰቡን ጠቁመዋል።

የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ስርዓት ከሰኔ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑ ይታወቃል።

ምንጭ – የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button