ማህበራዊ ጉዳይዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ የአለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ተጠልለው ለሚገኙ ስደተኞች የምግብ እርዳታ አቅርቦት መጀመሩን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29/2016 .ም፡ የአለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ተጠልለው ለሚገኙ የጎረቤት ሀገራት ስደተኞች የምግብ እርዳታ አቅርቦት መጀመሩን አስታወቀ። ዘጠኝ መቶ ሺ ለሚሆኑ በኢትዮጵያ ተጠልለው ለሚገኙ ስደተኞች የምግብ እርዳታ በማቅረብ ስራ መጀመሩን የመንግስታቱ ድርጅት በድረገጹ አስነብቧል።

በተለያዩ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ የምግብ እርዳታ አቅርቦቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ያስታወቀው ድረገጹ በተለይም በእርስ በርስ ግጭት በመታመስ ላይ ካለችው ሱዳን ተሰደው በኢትዮጵያ መጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ አዲስ ስደተኞች ለመጀመሪያ ግዜ እርዳታ አንዳገኙ አመላክቷል።

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 35ሺ የሚሆኑ የሱዳን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን እና አስቸኳይ የምግብ እርዳታ አቅርቦት እንደሚያስፈልጋቸው ያስታወቀው የመንግስታቱ ድርጅት የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ከ850ሺ በላይ ከሶማሊያ፣ ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን ተሰደው የመጡ ስደተኞች እንደሚገኙ ጠቁሟል።  

የምግብ እርዳታ አቅርቦቱ በተቋረጠባቸው መጠለያዎች ላይ በተደረገ የምግብ ደህንነት ጥናት የስደተኞቹ የምግብ ደህንነት ማሽቆልቆሉን የጠቆመው የተቋሙ መግለጫ የምግብ ደህንነታቸው በማሽቆልቆሉ ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ በመጠለያዎቹ ላይ ከፍተኛ የውጥረት ድባብ መስፈኑን አመላክቷል።

በሀገሪቱ በሚገኙ መጠለያ ካምፖች ውስጥ የሚገኙ 24 ማከማቻ ቦታዎችን የአለም የምግብ ፕሮግራም በብቸኝነት እያስተዳደራቸው እንደሚገኝ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተጎጂዎች ተብሎ የሚቀርብ እርዳታ ላልታለመለት አላማ እየዋለ መሆኑ በመረጋገጡ የመንግስታቱ ድርጅት የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ የሚያካሂደውን የእርዳታ አቅርቦት ባሳለፍነው አመት ሰኔ ወር ላይ ማቋረጡን መዘገባችን ይታወሳል። 

በተመሳሳይ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤድ በኢትዮጵያ አቋርጦት የነበረውን የምግብ እርዳታ አቅርቦት ከአራት ወራት በኋላ እንደሚጀምር ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል። የእርዳታ እህል አቅርቦቱ የሚጀምረው በሀገሪቱ ተጠልለው ለሚገኙ የጎረቤት ሀገራት ስደተኞች ብቻ መሆኑን ማስታወቁን በዘገባችን ተካቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የረድኤት ተቋሙ የእርዳታ አቅርቦቱን ለማስጀመር ውሳኔ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ተጠልለው ለሚገኙ የጎረቤት ሀገራት ስደተኞች ላይ ለሚካሄደው የእርዳታ ማጓጓዝ፣ ማከማቸት እና ማከፋፈል ዙሪያ ምንም አይነት ተሳትፎ እንደማይኖረው ስምምነት ላት በመደረሱ መሆኑን የዩኤስኤድ ቃል አቀባይ መግለጻቸውም ተመላክቷል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button