ዜናፖለቲካ

ዜና፡ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ በተወሰኑ ሰዎች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ያስተላለፉትን የብሄራዊ አደጋ ጊዜ ድንጋጌ ትዕዛዝ ዳግም አደሱ


አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 3/2015 ዓ.ም፡- የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ ከተከሰተው የሰብአዊ እና የሰብአዊ መብቶች ቀውስ ጋር በተያያዘ በተወሰኑ ሰዎች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል አስተላልፋው የነበረውን የብሄራዊ አደጋ ጊዜ ድንጋጌ ትዕዛዝ ዳግም አደሱ። 

ፕሬዝዳንት ባይደን ከሁለት አመት ቢፊት አ.አ.አ መስከረም 17፣ 2021 ተፈፃሚ እዲሆን ያስተላለፉት ትዕዛዝ በአማራ፣ አፋር እና ትግራይ ክልሎች አጋጥሞ በነበረው ጦርነት ወቅት ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱ “ብሔርን፣ ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት እና የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተጓጎልን ጨምሮ የተስፋፋ ግጭት፣ ግድያ፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የተከናወነበት በመሆኑ ለአሜሪካ መንግስት ብሔራዊ ደህንነትና ለውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስጋት ሆኗል። ይህንንም ስጋት ለመቋቋም ብሔራዊ አደጋ ጊዜ ድንጋጌ ትዕዛዛት አውጃለሁ” ብለዋል።

ይህንንም ትዕዛዝ ዳግም በማደስ ነጩ ቤተ መንግስት ኢትዮጵያ “በአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት እና ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ያልተለመደ ስጋት ማሳረፏን ቀጥላለች፡፡ በዚህም ምክንያት፣ መስከረም 17፣ 2021 የተወሰነው ትዕዛዝ ከመስከረም 17፣ 2023 በኋላ ተግባራዊ መሆን መቀጠል አለበት” ብሏል፡፡

በ2021 በትዕዛዙ ከተዘረዘሩት ሁኔታዎች መካከል አሜሪካ ግጭትን በድርድር ለማቆም እና ለጦርነቱ ፖለቲካዊ እልባት ለመስጠት፣ የኤርትራ ኃይሎች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ እና በሀገሪቱ አንድነት እና መረጋጋት ለማስፈን በሚደረግ ጥረት ላይ ድጋፍ እንደምታደርግ የተገለጸው ይገኝበታል፡፡

ለሁለት አመታት የዘለቀው አስከፊ ጦርነት ህዳር 2022 በፌደራል መንግስት እና ህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ በደረሱት የሰላም በስምምነት ቢያበቃም የፌዴራሉ መንግስት እስካሁን ድረስ በትግራይ ኢሮብ ወረዳ የጦር ወንጀልን ጨምሮ ጠለፋ እና ፆታዊ ጥቃት በማድረስ ላይ ያሉትን የኤርትራን ኃይሎች ለቀው እንዲወጡ አላደረገም፡፡

አሜነስቲ ኢንተርናሽናል ነሃሴ 30 ባወጣው ሪፖርት በፌደራል መንግስቱ እና በትግራይ ሀይሎች መካከል በፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የኤርትራ ኃይሎች አስገድዶ መደፈር፣ ግድያዎች፣ የጾታዊ ግንኙነት ባርነትን ጨምሮ የጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀም ፈጽመዋል ሲል ገልጧል፡፡ ወንጀሎቹ በዋናነት የተፈፀሙት በኤርትራ ድንበር አቅራቢያ በኮከበ ጽባህ እና ማርያም ሸዊቶ መሆኑንም አክሎ መግለፁ ይታወቃል፡፡አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button