ቢዝነስዜና
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ የአፍሪካ ልማት ባንክ በምስራቅ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማሻሻል የሚውል የ104 ሚሊየን ዶላር ብድር እና እርዳታ ፈቀደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3/2016 .ም፡ የአፍሪካ ልማት ባንክ በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚገኙ አከባቢዎችን የሀይል አቅርቦት ለማሻሻል ያግዛል ያለውን 104 ሚሊየን ዶላር ብድር እና እርዳታ ማጽደቁን በድረገጹ ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል።

የልማት ባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ካጸደቀው 104 ሚሊየን ዶላር ውስጥ 52 ሚሊየን ዶላሩን የአፍሪካ ልማት ባንክ በድጋፍ መልክ የሰጠው ሲሆን ቀሪው 52 ሚሊየን ዶላሩ ደግሞ የባንኩ የብድር አጋር ከሆነው ከኮሪያ የኢኮኖሚ ልማት ትብብር ፈንድ ያገኘው እና ለኢትዮጵያ እጅግ አነስተኛ በሆነ ወለድ እንድትበደረው የተደረገ መሆኑን መግለጫው አመላክቷል።

ከአፍሪካ ልማት ባንክ የተገኘው 104 ሚሊየን ዶላር በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚገኙ አነስተኛ ማሳ ለሚያለሙ አርሶ አደሮች፣ በከብት ማርባት ለተሰማሩ ገበሬዎች፣ በአከባቢው የሚገኙ ፋብሪካዎችን እና ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ያለው መግለጫው በአከባቢው የሚገኙ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያዎችን በማሻሻል ተጠቃሚነታቸው እንዲያድግ ያደርጋል ብሏል።

የምስራቅ ኢትዮጵያ ክፍል አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለታዳሽ ሀይል እንዲያገኝ ያስችላቸዋል ሲሉ የልማት ባንኩ የሀይል አቅርቦት ልማት ዳይሬክተር ባቺ ባልዴህ መናገራቸውን ያካተተው መግለጫው ተጨማሪም በአከባቢው የሚገኙ በርካታ ከተሞች በነዳጅ የሚሰሩ ጀኔረተሮችን በማስቀረት የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት እንዲሟላላቸው ያስችላል ማለታቸውን ጠቁሟል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ በአከባቢው መንግስት በመስኖ ለማልማት ያሰበውን ግማሽ ሚሊየን ሄክታር የሚደርስ መሬትን ለማስጀመር ያስችለዋል ያለው መግለጫው በዚህም አከባቢው በምግብ እራሱን እንዲችል ለሚደረገው ጥረት ወሳኝ ነው ብሏል።

ፕሮጀክቱ በተጨማሪም የ400 ኪሎ ቮልት ተሸካሚ የሚሆነውን እና 157 ኪሎሜትር የሚሸፍነውን የኤሌክትሪክ መስመር በማሻሻል እና በሀረር፣ ጂግጂጋ እና ፋፌም ከተሞች የሚገኙ ሰብ ስቴሽኖችን ማሻሻልን እንደሚጨምር አመላክቷል። የኤሌክትሪክ መስመሩ እና የሰብ እስቴሽኖቹ መዘመን ሀገሪቱ በቀጠናው በተለይም ከሶማሊያ ለሚኖራት የኤሌክትሪክ ትስስር ማስጀመሪያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው ሲል መግለጫው አትቷል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button