ዜናፖለቲካ

ግብጽ በግዙፍ ወታደራዊ መርከብ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለሶማሊያ ማድረጓ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13/2017 ዓ.ም፡- ከፍተኛ ቁጥር ያለው ከባድ መሳሪያዎች እና ፀረ-ታንክ ሚሳኤሎች የጫነ የግብጽ ግዙፍ ወታደራዊ የጭነት መርከብ ሞቃዲሾ ወደብ መድረሱ ተገለጸ።

በቪዶዮ በማስደገፍ በርካታ የሶማሊያ መገናኛ ብዙሃን ባሰራጩት ዘገባ አንድ የግብፅ ወታደራዊ ጭነት መርከብ ከፍተኛ ቁጥር ያለው መሳሪያ በሞቃዲሾ ወደብ ትላንት መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም ማራገፉን አመላክተዋል፤ ወታደራዊ መርከቡ ጭነቱን እንዲያራግፍ በሚል ወደቡ ለንግድ መርከቦች ዝግ ተደርጎ እንደነበርም ጠቁመዋል።

ከባለፈው አመት 2016 ዓ.ም ታህሳስ ወር ላይ የተባበሩት መንግስታት የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ከተነሳ በኋላ ለሶማሊያ ከፍተኛው ወታደራዊ ዕርዳታ ነው ሲሉ ዘገባዎቹ አስታውቀዋል።

ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት ጠይቆ ማግኘት እንዳልቻለ ሮይተርስ የዜና ወኪል በጉዳዩ ዙሪያ ባሰራጨው ዘገባ አመላክቷል።

ይህ የግብጽ እንቅስቃሴ በሶማሊያ የምታደርገውን ወታደራዊ ተሳትፎ እየተጠናከረ መምጣቱን ያሳያል ያሉት መገናኛ ብዙሃኑ ውጥረት በሰፈነበት የአፍሪካ ቀን ላይ ስጋት የሚያጭር ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የግብጽ የመሳሪያው ድጋፍ በቅርቡ በካይሮ እና በሞቃዲሾ መካከል የተደረሰው የመከላከያ ስምምነት አካል መሆኑን የጠቆሙት መገናኛ ብዙሃኑ ይህ ጭነት ግብፅ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ተፅእኖ ለማሳደግ የምትከተለውን ​​ስትራቴጂ የሚያንጸባርቅ ነው ብለዋል፤ በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር በአባይ ወንዝ ሳቢያ ያላትን ፍጥጫ በበላይነት ለመቆጣጠር በሚል የሶማሊያን የመከላከል አቅም ለማጠናከር ያለመ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የግብጽ ወታደራዊ መርከብ ሞቃዲሾ ወደብ ላይ ሲደርስ የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር እና የሀገሪቱ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት አቀባበለ ማድረጋቸውን ዘገባዎቹ አስታውቀዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ እና የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ በካይሮ በቅርቡ የተፈራረሙትን የመከላከያ ስምምነት ተከትሎ ከአንድ ወር በፊት ነሃሴ 2016 ዓ.ም c-130 የተባሉ ሁለት የግብፅ ወታደራዊ አውሮፕላኖች በአደን አዴ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማረፋቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ግብጽ ወታደሮቿንና የጦር መሳሪያዎችን በሶማሊያ ያሰማራችው በቅርቡ በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መካከል የተፈረመው የባህር በር የመግባቢያ ስምምነትን ተከትሎ በቀጠናው ውጥረት በነገሰበት ወቅት ነው።

በሶማሊያ የግብፅ ኃይል መገኘት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ላለው አለመግባባት እና በአፍሪካ ቀንድ ለሚኖረው ፍላጎቶች እንደ ስትራቴጂካዊ እርምጃ ተደርጎ ይወሰዳል ሲል የፑትላንዱ ጋሮዌ ኦንላይን በወቅቱ መዘገቡ ተካቷል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነሃሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም “በአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ሁኔታ” ዙሪያ በሰጠው መግለጫ “የሶማሊያ መንግስት ሰላም ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶች ከማጠናከር ይልቅ ቀጠናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል” ሲል መተቸቱን መዘገባችን ይታወሳል።

በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) በቀጣይ የሚኖረው አዲስ የሰላም ተልዕኮ አወቃቀር ሁኔታ “በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ላይ አዲስ ስጋት ይዞ መምጣቱ ኢትዮጵያን የሚያሳስብ ሆኗል” ያለው መግለጫው “ቀጠናው ሊተነበይ ወደማይቻል ፈተና ውስጥ እየገባ ይገኛል” ሲል ማስታወቁም በዘገባው ተካቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button