ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ በሀዲያ ዞን ከ300 በላይ የሆስፒታል ሠራተኞች የማቆም አድማ እያደረጉ መሆኑን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16/ 2016 ዓ/ም፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን ሾኔ ከተማ ከ300 በላይ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሠራተኞች፤  ለሁለት ወር ደመወዝ ባለመከፈሉ ምክንያት ካለፈው ሳምንት አርብ ጀምሮ ስራ የማቆም አድማ እያደረጉ መሆኑን ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ሰራተኞች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ። 

“የወር ደመወዝ እየተከፈለን ባለመሆኑ ለልጆቻችን አስፈላጊ የሆኑ ቁሶችን ለማሟላት እንዲሁም ምግብ እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ለማቅረብ እየተቸገርን ነው። ደመወዛችን እንዲከፈለን በመጠየቅ አድማ እያደረግን ነው” ሲሉ አንድ የህክምና ባለሙያ ተናግረዋል።

የግንቦት እና የሰኔ ወር ደመወዝ እንዳለተከፈላቸው የገለጹት የአድማው ተሳታፊ፤ የሆስፒታሉ አመራሮችና አስተዳደሮች የግንቦት ወር ደመወዝ ሳይከፍሉ የሰኔን ብቻ እንዲከፈለን በማድረግ ላይ ናቸው በለዋል። በርካታ ሰራተኞች ይህን ተቃውመዋል ሲሉም ገልጸዋል።

የሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር መሀመድ አህመድ የሰራተኞች ክፍያ መዘግይት በሆስፒታሉ ስራ ላይ ተጽዕኖ እያደረሰ መሆኑን ለአዲስ ስታንዳርድ አስረድተዋል።

የባድዋቾ ወረዳ የፋይናንስ አስተዳዳሪ የሰራተኞችን ቁጥር ለመለየት የሚጥይቅና ደብዳቤ መጻፉንና ደመወዛቸውን ከተቀበሉ በኋላ ብቻ ፔሮል ላይ እንዲፈርሙ መመሪያ ሰጥቷቸዋል በለዋል። ይሁን እንጂ ሠራተኞቹ ይህን ትዕዛዝ ውድቅ በማድረግ የሁለት ወር ደመወዛቸውን ከተቀበሉ በኋላ ብቻ እንደሚፈርሙ ተናግረዋል።

የሆስፒታሉ አመራር የደመወዝ ክፍያ ጉዳዮች ለሃዲያ ዞን አስተዳዳሪ እና ለመዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ቢያሳውቅም፣ በወረዳ እና በክልል ደረጃ የጥሬ ገንዘብ ፍሰት እጥረት እንዳለ ተነግሯል ተብሏል።

ከዚህ ቀደም በዞኑ የወር ክፍያ ችግር የተነሳ በርካታ መምህራንና የህክምና ባለሙያዎች የስራ ማቆም አድማና የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸውን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቡ ይታወሳል። ሰላፉን ተከትሎም በርካታ መምህራን ለእስር እና ማስፈራሪያ መዳረቻቸውን ተገልጿል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ታህሳስ 13፣ 2016 ዓ/ም፡ ባወጣው መግለጫው በሃዲያ ዞን ከደመወዝ ጋር የተያያዙ ችግሮች ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ የሚስተዋል መሆኑን እና ከችግሮቹ መካከልም በየወሩ መጨረሻ ሊከፈል የሚገባው ደመወዝ ከ10 እስከ 20 ቀን እንደሚዘገይ እና በተለያዩ ወቅቶች መከፈል ከነበረበት ሙሉ ደመወዝ 30፣ 50 እና 70 በመቶው ብቻ ሲሰጥ መቆየቱን የሚያጠቃልል መሆኑን ገልጿል። 

ኢሰመኮ “ችግሩ ተባብሶ በዋናነት ከፖሊስ፣ ፍርድ ቤቶች እና ፍትሕ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች በስተቀር በአብዛኛው የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ደመወዝ ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ በመቆየቱ ለዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ቀውስ መዳረጋቸውን ሰራተኞቹ ገልጸዋል” በሏል።

በሃዲያ ዞን አከባቢዎች ከደመወዝ አለመከፈል ጋር ተያይዞ ቅሬታ እና ተቃውሞ ባሰሙ ሰዎች ላይ ማስፈራራት፣ ዛቻ፣ ድብደባ እና ለተለያዩ ጊዜያት እስራት ጭምር ደረሶባቸዋል ያለው ኢሰመኮ ሁሉም የክልል መስተዳድሮች ተገቢ የማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድ ለሠራተኞች ደመወዝ ወቅቱን ጠብቆ መከፈሉን እና ሰብአዊ መብቶቹ መከበራቸውንና መጠበቃቸውን ሊያረጋግጡ ይገባል ሲል ማሳሰቡ ይታወሳል።አስ 

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button