ዜናፖለቲካ

ዜና: በሀገራዊ ምክክር ሂደት ባለ ድርሻ አካላት ካልተሳተፉ ሂደቱ እንደማይሳካ የሀገራት ተሞክሮ ያሳያል ሲል ኮሚሽኑ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10/ 2016 ዓ/ም፦ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ጉልህ ሚና ያላቸው ባለ ድርሻ አካላት ካልተሳተፉ የምክክር ሂደቱ እንደማይሳካ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ያሳያል ሲል የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ፡፡ 

ኮሚሸነር ዶ/ር ዮናስ አዳዬ ለሽገር ሬድዮ እንደገለጹት በምክክር ሂደት ውስጥ ጉልህ ድርሻ ሊኖራቸው የሚችሉ ባለድርሻ አካላት በአግባቡ ተደራጅተው ሀሳባቸውን ማቅረብ ሳይችሉ ሲቀሩ እንዲሁም አንዳንድ ቡድኖች በሂደቱ ውስጥ ለመሳተፍ ዝቅተኛ ፍላጎት አሊያም ሙሉ ለሙሉ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ከቀሩ የምክክር ሂደቱ ውጤት ላያመጣ እንደሚችል የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ያስረዳል ብለዋል።

ኮሚሽነሩ በምክክር ሂደት ውስጥ ያለፉ ሀገራት ውጤታማ እንዳይሆን ከሚያስችሉ ምክንያቶች ቀዳሚው በተለያዩ ቡድኖች መካከል እጅግ ሰፊ የሆነ የሃይል አለመመጣጠን ሲኖር እና የገነኑ ሀይሎች አቅማቸውን ተጠቅመው የሀገራዊ ምክክሩን የማስቀየር አዝማሚያ ሲያሳዩ ነዉ ብለዋል፡፡  

ይህ በእንዲህ እያለ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በቀጣይ ሳምንት በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በሐረሪ እና በድሬዳዋ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት እንደሚጀምር የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።  ስራውን ለማስተባበር የኮሚሽኑ ሙያተኞችና ኮሚሽነሮች ወደ አካባቢዎቹ ስምሪት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ስራውን ለመጀመር ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ጋር በተያያዘ ቀሪ ስራዎች እስከሚጠናቀቁ እየተጠባበቀ መሆኑንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

አጀንዳ የማሰባሰብ ክንውኑ በአብዛኞቹ ክልሎች እስከ ነሐሴ 30/2016 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሰራ ስለመሆኑ የገለጹት ኮሚሽነሩ በአፋር ክልል ያለው ወቅታዊ የአየር ሁኔታ ከባድ ሙቀት ያለበት በመሆኑ፤ በክልሉ የሚከናወነው አጀንዳ ማሰባሰብ ጥቅምት አካባቢ እንደሚካሄድ ይፋ አድርገዋል።

ኮሚሽኑ፤ በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ ታጣቂዎች በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የመሳተፍ ፍላጎት ካላቸው ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲሳተፉ አደርጋለሁ ሲል በመግለጫው ገልጿል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በምክክር ሂደቱ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ አካላት የመሳተፍ ፍላጎት ካላቸው ደንነታቸው ተጠብቆ እንዲሳተፉ የማድረግ አቅሙ አለኝ ሲል ኮሚሽኑ አስረድቷል፡፡

ምንም እንኳ ኮሚሽኑ ይህን ቢልም በሂደቱ “አካታችነት እና ገለልተኛነት” ላይ እንዲሁም የኮሚሽነሮቹ ምርጫ ላይ ትችት ሲሰነዘርባቸው ቆይቷል።

በኦሮሚያ ክልል፤ ትልቅ ተጽዕኖ ያላቸው ታወቂዎቹ ሁለት ፓርቲዎች ማለትም የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ(ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን (ኦነግ) ጨምሮ በርካታ ፓርቲዎች በሂደቱ ላይ ለመሳተፍ ፍቃደኛ ባለመሆነቸው የኮሚሽኑ ቅቡልነት ላይ ጥርጣሬ አስከትሏል።

አዲስ ስታንዳርድ በየካቲት ወር ርዕሰ አንቀጹ ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን በሀገሪቱ የሚንቀሳቃሱ ዋነኛ የታጠቁ እና ያልታጠቁ ተቃዋሚ ቡድኖችን ማሳተፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጿል። በአሁኑ ወቅት ከመንግስት ሃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ የሚገኙትን እንደ ኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ያሉ የታጠቁ ሃይሎችን አለማካተት የምክክሩን ቅቡልነት እና ግጭት መንስዔዎችን ለመቅረፍ የሚያስችለውን አቅም አንደሚያዳክም ርዕስ አንቀጹ ያትታል። 

በኦሮሚያ ክልል ዋና የሚባሉት ፓርቲዎች ማለትም የኦሮሞ ፌዴራሊስት ፓርቲ (ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ( ኦነግ) መሳተፍ እንዳለባቸው አክሎ ገልጿል። ኮሚሽኑ ከተለያዩ ቡድኖች የተውጣጡ ተሳታፊዎችን ለይቶ ማወቁን ቢገልፅም ርዕሰ አንቀጹ በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ክልሎች እየተካሄዱ ባሉ ግጭቶች ምክንያት ተግዳሮቶችን መኖራቸውን ገልጿል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button