ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ ምዕራብ ጎጃምና ሰሜን ጎጃም ዞኖች የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናን እንደማያስፈትኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3/ 2016 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል የዘንድሮው የ8ኛ ክፍል ፈተና ከነገ ሰኔ 4 እስከ 5 ቀን 2016 ዓ.ም የሚሰጥ ሲሆን  የ6ኛ ክፍል ፈተና ከሰኔ 13 እስከ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ይሰጣል። 

በክልሉ ባለው የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት ይህን ክልላዊ ፈተና በምዕራብና ሰሜን ጎጃም ዞኖች እንደማይሰጥ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል። 

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊና የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ዶ/ር ሙሉነሽ ደሴ ትላንት በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ በጸጥታ ችግር አመቱን ሙሉ በምዕራብ ጎጃምና ሰሜን ጎጃም ትምህርት ያልተማሩ ተማሪዎች መኖራቸውን ገልጸው ተፈናም እንደማይሰጥ ገልጸዋል።

በቀጣይ ሁለተኛ ዙር ፈተና ተመቻችቶ እና ታቅዶ ፈተናውን እንዲወስዱ ይደረጋል ያሉት ኃላፊዋ፤ ከ354 ሺህ በላይ የ6ኛና 8ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች በሌሎች አንፃራዊ ሰላም ባለባቸው ዞኖች እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

የምስራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ አጠቃላይ ካሉ 996 አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች፤ ከነውስንነቱም ቢሆን የመማር ማስተማር ስራቸውን እያከናወኑ የሚገኙት 32 ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆናቸውን አስታወቋል።

በትምህርት ዘመኑ ከአንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ከ539,996 በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንደሚመጡ ቢታቀድም ወደ ት/ቤት መምጣትና ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት ከ13,000 የሚበልጡ አይደሉም ነው የተባለው።

በበጀት አመቱ 791 ት/ቤቶች ከ41,944 በላይ ተማሪዎች  የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና እንደሚያስፈትኑ ቢጠበቅም 12 ት/ቤቶች  በሁለት ዙር 506 ተማሪዎችን ብቻ እንደሚያስፈትን መምሪያ ገልጿል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተጨማሪም 593 ት/ቤቶች 38,203 ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ፈተና እንደሚወስዱ ቢታቀድም በ10 ት/ቤቶች  431 ተማሪዎች ብቻ በሁለት ዙር ፈተና የሚወስዱ ይሆናል። እንዲሁም 65 ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ከ19,657 በላይ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ሃገር-ዓቀፍ ፈተና እንደሚወስዱ ቢታሰብም 5 ት/ቤቶች 577 ተማሪዎችን ብቻ በሁለት ዙር የሚያስፈትኑ ይሆናል ተብሏል።

በክልሉ የተፈጠረው ግጭት ት/ቤቶች እንዲዘጉና ለሌላ ዓላማ እንዲውሉ ያደረገ፤ ተማሪዎችንና ማህበረሰቡን  በስነልቦና ያኮሰሰ፤ በትውልድ ግንባታ ስራው ላይ ከፍተኛ ማነቆ የፈጠረና ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የትምህርት ማህበረሰብ አባላትን ከመደበኛ ስራቸው ውጭ ያደረገ ክስተት ሁኗል ሲል ምስራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም ከ407 በላይ ት/ቤቶች እንዲወድሙና ለመማር ማስተማር አገልግሎት እንዳይሰጡ መሁኑንና በዚህም ከ290.3 ሚሊዮን በላይ የት/ቤቶች ሀብትና ንብረት መውደሙን አክሎ አስታውቋል።

ከክልሉ ወቅታዊ የፀጥታ መደፍረስ ጋር በተያያዘ በዚህ ዓመት መመዝገብ ከነበረባቸው 6. 2 ሚሊዮን ተማሪዎች መካከል የተመዘገቡት 4 ሚሊዮኑ ብቻ መሆናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button