በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ፍርድ ቤት አለመቀረባቸው ተገለጸ፤ የህዳር 30 ሠልፍ አስተባባሪ አቶ ዘለሌ ጸጋስላሴ ታሰሩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29/2016 ዓ/ም፦ ባሳለፍነው ሳምንት አርብ ግንቦት 23 ቀን 2016 በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የቀድሞ የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ፍርድ ቤት አለመቀረባቸው ተገለጸ።  

“ጦርነት ይቁም! ሰላም ይስፈን!” በሚል መሪ ቃል ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት የሰለፉ አስተባባሪዎች መካከል አንዱ ከሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ በተጨማሪ አቶ ዘለሌ ጸጋ ስላሴ ትናንት ግንቦት 28 ቀን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሰልፉ አስተባባሪ የሆኑት ይስሀቅ ወልዳይ ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጸዋል። 

ከአርብ ግንቦት 23 ቀን ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት የሠልፍ አስተባባሪና የቀድሞ የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ “ፋኖን ሊደግፍ የሚችል ጽሁፍ በሚዲያ ጽፈዋል” የሚል ክስ በቃል ከፖሊስ እንደቀረበላቸው አቶ ይስሀቅ ገልጸዋል።

አቶ የሺዋስ አሰፋ “ሁከት በማነሳሳት” መጠርጠራቸውን ባለቤታቸው ወ/ሮ ሙሉ ብርሃን ለአዲስ ስታንዳርድ መግለጻቸው ይታወቃል።

ይህ በእንዲህ እያለ ህዳር 30 የተጠራው ሰልፍ አስተባባሪ የነበሩት አቶ ዘለሌ ጸጋ ስላሴ ትላንት ግንቦት 28 ቀን 2016 መሳለሚያ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተይዘው መታሰራቸውን ይስሀቅ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። 

“አቶ ዘለሌ ጸጋስላሴ ትናንት ረፋድ ተይዘዉ አመሻሹ ደሞ ወደ ቤታቸዉ ተወስደዉ ብርበራ ተደርገዋል። በብርበራዉ በቤታቸዉ የነበረዉ የቀድሞ የኢትዮጵያ ባንዴራ (ኮከብ የሌለዉ)፣ የባልደራሰ ፓርቲ አርማዎች እና ፕሮግራምች እንዲሁም በምስረታ የነበረዉ የአማን ፓርቲ የአባላት ፊርማዎች እና አንዳንድ ፅሁፎች ተይዞባቸዋል።” ሲሉ አቶ ይስሀቅ ገልጸዋል። 

“በመንግስት ጫና የሠልፉን እንቀስቃሴ ብናቆምም በርካታ አስተባባሪዎች እየታሰሩ ነው” ሲሉ የተናገሩት አቶ ይስሀቅ፤ አስተባባሪዎቹ “ለፋኖ ድጋፍ ታደጋላችሁ” የሚል ክስ ሲቀርብባቸው እንደቆየ ገልጸዋል። ባሁኑ ወቅት ከአስተባባሪዎቹ መካክል ያለታሰሩ ሶስት ፖለቲከኞች ብቻ መሆናቸውን አክለው ተናግረዋል። 

“ጦርነት ይቁም! ሰላም ይስፈን!” በሚል መሪ ቃል ህዳር 30 ሊካሄድ የነበረው ሰልፍ “በመንግስት ጫና” ምክንያት ላልታወቀ ግዜ መራዘሙን የሰልፉ አስተባባሪ የሆኑት አቶ የሺዋስ በወቅቱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።

የሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴው የሰልፉ አላማ በአገራችን ጦርነት እንዲቆም በማድረግ የሚደርሰውን እልቂትና ውድመት ማስቀረት፣ የፖለቲካ ልዩነቶች በሰላም እንዲፈቱ በማለም እንደነበር ገልጿል። ነገር ግን የጋራ ግብረ- ኃይል ህዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “በሰላማዊ ሰልፍ ሽፋን አዲስ አበባን የሁከትና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ የሽብር ተልዕኮ ተቀብለው በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖች ሴራ አክሽፊያለሁ” ሲል መግለጹ ይታወሳል። አስ

Exit mobile version