እለታዊ ዜና፡ መርማሪ ቦርዱ በባህርዳር ማረሚያ ቤት መምሪያ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን ጎበኘ፤ የሚታዩ ጉድለቶች እንዲታረሙ አሳስቧል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 30 / 2015 ዓ.ም፡- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አባላት በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ማረሚያ ቤት መምሪያ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን መጎብኘቱ ተገለፀ። ቦርዱ ባደረገው ጉብኝት ከተጠርጣሪዎች ጋር ውይይት በማድረግ በተጠርጣሪዎች አያያዝ ዙሪያ የተመለከታቸው መልካም ነገሮች እንዲጠናከሩ እና የሚታዩ ጉድለቶች እንዲታረሙ አሳስቧል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ የቦርዱ ሰብሳቢ አዝመራው አንዴሞ በጉብኝቱ ከተጠርጣሪዎች ጋር ስላለው ሰብአዊ መብት አያያዝ ውይይት በማድረግ መረጃ መሰብሰባቸውን ገልጸዋል። ተጠርጣሪዎች ወደ ማረሚያ ቤቱ ከመተላለፋቸው በፊት ስለነበራቸው ቆይታ በውይይቱ ወቅት ማንሳታቸውን ጠቁመው፤ መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮች እንዳነሱላቸውም ገልፀዋል ተብሏል።  

ሰብሳቢው መኝታ፣ መታጠቢያ፣ ባኞ ቤት እና አስፈላጊ የሚባሉ ግብዓቶች በማረሚያ ቤቱ መኖራቸውን ጠቅሰው ተጨማሪ ህክምና ለሚያስፈልጋቸው ማረሚያ ቤቱ አስፈላጊውን እንዲያደረግ ምክረ ሃሳብ ማቅረባቸውንም ገልጸዋል። ተጠርጣሪዎቹ እንዲሟሉ የጠየቋቸውን ጉዳዮች እንዲሟሉ ከሚመለከተው አካል ጋር እንደሚመክሩ ጠቁመዋል።

ከመርማሪ ቦርድ አባላቱ ጋር የተወያዩት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ እና የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ሌተናል ጀነራል ብርሃኑ በቀለ፤ ተጠርጣሪዎች ወደ ማረሚያ ቤት ከመላካቸው በፊት ከሰራዊቱ ጋር እንዲቆዩና ህክምና የሚያስፈልጋቸውም እንዲታከሙ መደረጉን ገልፀዋል ነው የተባለው።

ተጨማሪ አልባሳት መሟላትን ጨምሮ ሌሎች ግብዓት እንዲሟሉም ያሳሰበው መርማሪ ቦርዱ፤ በባህርዳር ከተማ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ መብት አያያዝ መልካም የሚባል ስለመሆኑም አስታውቋል።አስ

Exit mobile version