ማህበራዊ ጉዳይዜና

ዜና፡ እስካሁን ድረስ ስምንት ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም፤ የአስክሬን ፍለጋው ቀጥሏል_ የገዜ ጎፋ ወረዳ ኮሚኒኬሽን ሃላፊ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22/ 2016 ዓ/ም፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ባሳለፍነው ሳምንት በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ እስካሁን ስምንት ሰዎች አስክሬናቸው አለመገኘቱን የገዜ ጎፋ ወረዳ ኮሚኒኬሽን ሃላፊ ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።

የኮሚኒኬሽን ሃላፊው አቶ የዓለም መርህነህ እንደገለጹት በመጀመሪያው የመሬት ናዳው አደጋ ተጎጂ የነበሩ አንድ ግለሰብ አስከሬን በትላንትናው እለት የተገኘ ሲሆን የእሳቸውን ልጅ ጨምሮ በአጠቃላይ ስምንት የሚደርሱ የአደጋው ሰለባዎች እስከአሁን የገቡበት አለመታወቁን ተናግረዋል።

ከ250 በላይ ሰዎችን ህይወት በቀጠፈው የመሬት ናዳ አድጋ፤ ደብዛቸው የጠፉ ሰዎችን አስክሬን ፍለጋ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት አቶ የዓለም መርህነህ ከአስከሬን ፍለጋው ጎን ለጎን ሁሉም የአከባቢው ማህበረሰብ በተገኘበት የሻማ ማብራት ሥነ ስርዓት በዛሬው ዕለት እንደሚከናወን ገልጸዋል::

“ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን በዘላቂነት ወደ ሌላ ቦታ ለማስፈር ርብርብ እየተደረገ ነው” ያሉት የኮሚኒኬሽን ኃላፊው አክለውም በመሬት ጥናት ባለሙያዎች ለአደጋ ተጋላጭ ተብለው በተለዩ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሰዎች ተለዋጭ ቋሚ ቦታ ለማግኘት በርካታ ጥናቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል። 

የጥናት ቡድኑ ጥናቱን አጠናቆ ቋሚ ቦታ እስኪዘጋጅ ድረስም የአከባቢውን ማህበረሰብ በቅርብ ወደተዘጋጁ መጠለያዎች እንዲሰፍሩ እየተደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በክረምቱ እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ የተነሳ ተጨማሪ አደጋዎች እንዳይከሰቱ የቦይ ተፋሰስ ልማት እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት የኮሚኒኬሽን ሃላፊው አክለውም ለተጎጂዎች እርዳታ እና ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል::

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ የተከሰተውን የመሬት ናዳ ተከትሎ በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ አደጋ እያጋጠመ ይገኛል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በሲዳማ ክልል ማዕከላዊ  ሲዳማ  ዞን ወንሾ ወረዳ ግሽሬ፤ ጉዱሞና ሆሞ ተብሎ የሚጠራ አከባቢ ትናንት ሐምሌ 21 ቀን በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት በተከሰተ የመሬት ናዳ የስድስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ስድስት ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል። 

በተመሳሳይ መልኩ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ በተከሰተ የመሬት ናዳ የ3 ሰዎች ህይወት አልፏል። 

በተጨማሪም በክልሉ ካፋ ዞን በተከሰተ ድንገተኛ የመሬት ናዳ አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 24 ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለሞቱ ዜጎች መታሰቢያ የሚሆን  ከሐምሌ 20 ቀን እስከ ሐምሌ 23 2016 ዓ/ም የ3 ቀናት ብሔራዊ ሃዘን መታወጁ ይታወሳል::

የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ቀበሌ በመገኘት በደረሰው አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን ማጽናናታቸው የሚታወስ ሲሆን የሩሲያ ፕሬዝታንት ቪላድሚር ፑቲንንና የተ.መ.ድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት መሪዎችም በአደጋው የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል:: አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button