Uncategorized
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: “ከታገቱ ተማሪዎችም መካከል የተወሰኑት የተጠየቀዉን ክፍያ ከፍለው ተለቀዋል” - ኢሰመጉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6/2016 ዓ.ም፡-የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ በታጣቂዎች ከታገቱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መካከል “የተወሰኑት ተማሪዎች የተጠየቀዉን ክፍያ መክፈል በመቻላቸው መለቀቃቸውን” አስታወቀ።

ከታገቱ ተማሪዎችም መካከል የተወሰኑት “በተለያዩ ምክንያቶች” ከአጋቾች ማስለቀቅ መቻሉን  ካሰባሰባቸው መረጃዎች መረዳቱን አመላክቷል፤ ምክንያቶቹን አላብራራም።

ብዛት ያላቸው ተማሪዎች አሁንም በአጋቾች ታግተው እንደሚገኙ ይህም ታጋቾችን ለከፍተኛ እንግልትና ስቃይ መዳረጉን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለማወቅ መቻሉን ጠቁሟል።

የታገቱ ተማሪዎች ተለቀዋል በሚል የሚናፈሰውን መረጃ በተመለከተ ኢሰመጉ በመግለጫው “ታጋቾች በተያዙበት ወቅት አጋቾቹ ተማሪዎችን በቡድን በቡድን በማድረግ ወደ ተለያየ አቅጣጫ ይዘዋቸው መንቀሳቀሳቸውን” ጠቁሞ የተለቀቁ ተማሪዎች እየሰጡ ያለው መረጃም “እነሱ በነበሩበት ቡድን ውስጥ ስላለው ሁኔታ ብቻ ነው” ሲል ጠቁሟል።

ከታገቱት አጠቃላይ ተማሪዎች ውስጥ ምን ያህል እደተለቀቁ የሚያሳይ አለመሆኑን አስታውቋል።

ኢሰመጉ የፌዴራል እና የክልል መንግስታት በግዛት ክልልቸው የሚፈጸመውን እገታ እና አስገድዳ መሰወር ለማስቆም በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ እንቅስቃሴ አላደረጉም ሲል ትላንት ሐምሌ 5 ቀን 2016 ዓ.ም “መንግስት በዜጎች ላይ የሚፈጸመውን እገታና አፍኖ መሰወር በአስቸኳይ ሊያስቆም ይገባዋል” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ ወቅሷል።

በዚህም ምክንያት በዜጎች ላይ የሚፈጸመው እገታና አፍኖ የመሰወር ተግባር በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ማህበረሰቡን ለከፍተኛ ምሬት እና እንግል እየዳረገው ይገኛል ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የፌደራል እና የሚመለከታቸው የክልል መንግስታት የግዛት ወሰናቸው ባሉባቸው አካባቢዎች የሚፈጸሙ የእገታና አፍኖ የመሰወር ድርጊቶችን እንዲያስቆሙ፣ የእገታና አፍኖ የመሰወር ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችን በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርጉ እና ለዜጎች ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርጉ ኢሰመጉ በመግለጫው ጥሪውን አቅርቧል።

መንግስት የታገቱ ተማሪዎች ተለቀዋል እያለ ሀሰተኛ መረጃ እያሰራጨብነው ሲሉ የታጋች ቤተሰቦቸ ማዘናቸውን መግለጻቸውን የተመለከተ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል።

“ከአጋቾቹ ጋር በየቀኑ እየተገናኘን ነው፣ አሁንም ገንዘቡን እንድንከፍል እየተጠየቅን ነው፣ ልመናችንንም እየሰሙ አይደለም” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀዋል፤ አክለውም አጋቾቹ ልጃቸውን ለመልቀቅ አንድ ሚሊዮን ብር እየጠየቁ መሆኑን የታጋች ቤተሰብ ነግረውናል።

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ ከተማ በተፈፀመው የተማሪዎች እገታ ዙሪያ የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ቢሮ ሃላፊው ሀይሉ አዱኛ ለመንግስትመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ እገታው የተፈጸመው በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ ብለው የጠሩት) ነው ሲሉ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

የኦሮምያ ክልል መንግስት የሰጠውን መግለጫ ተከትሎ ቡድኑ ሐምሌ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በዩኒቨርስቲ ተማሪዎቹ እገታ እጄ የለበትም ሲል ማስተባበሉ እና ለእገታው ተጠያቂ መሆን ያለበት መንግስት ነው መኮነኑም ይታወሳል።

ተጨማሪ አሳይ
Back to top button