ዜናቢዝነስ

ዜና፡ ለሽያጭ የቀረቡት የስኳር ፋብሪካዎች የጨረታ ሂደት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን እና በቅርቡ የተጫራቾች ዝርዝር ይፋ እንደሚደረግ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5/2016 .ም፡ የመንግስት የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ለማዞር የወጣው ጨረታ ሂደት እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ የፋይናንስ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በጨረታው የተሳተፉ አካላት የቴክኒክ ብቃት ልየታው መጠናቀቁን የፋይናንስ ሚኒስቴር ባሳለፍነዋ ሳምንት ማገባደጃ አስታውቋል። በጨረታው ከተሳተፉ አካላት ውስጥ ብቁ የሆኑ እና የቴክኒክ መስፈርቱን አሟልተው ያለፉት በተያዘው ሳምንት መጨረሻ እንደሚገለጽ ሚኒስቴሩ ጠቁሟል።

የስኳር ፋብሪካዎቹ በግልጽ ጨረታ ለሽያጭ ከቀረቡ አንድ አመት እንዳለፈው ይታወሳል።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በማህበራዊ ትስስር የፌስቡክ ገጹ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው የጨረታውን የቴክኒክ መስፈርት ያለፉት አካላት ይፋ ከተደረገ በኋላ ቀጣዩ ሂደት ተሳታፊዎቹ ያቀረቡትን የፋይናንስ ነክ ጉዳይ መረጃን መመልከት እና መመዘን መሆኑን አመላክቷል።

በጨረታው የተሳተፉ አካላት ዝርዝር በመንግስት ይፋ ባይደረግም ከሁለት ወራት በፊት መንግስት 20 የሚደርሱ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ተጫራቶች መሳተፋቸውን አስታውቋል። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት እንዳስታወቁት በጨረታው ከተሳተፉ አካላት መካከል ዳንጎቴ ስሚንቶ፣ ኮካኮላ የለስላሳ መጠጥ ፋብሪካ፣ የኢትዮጵያ የስኳር ማምረሻ ኢንደስትሪ እና አቢሲኒያ የቢዝነስ ግሩፕ ይገኙበታል።

በመንግስት ለጨረታ የቀረቡት የስኳር ፋብሪካዎችም ኩራዝ አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት እና አምስት፤ እንዲሁም አርጆ ደዴሳ፣ ከሰም እና ተንዳሆ መሆናቸው ይታወቃል። አስ  

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button